በትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዳማ ሚያዝያ 15/2012/ ኢዜአ፡- በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በደረሰው የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ በአዳሚ ቱሉ ወረዳ ሎቄ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ ነው ።
የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አአ 31359 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ጫት ጭኖ ከሻሻመኔ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እንዳለ ከሰሌዳ ቁጥር ኮድ3 ኦሮ 66004 የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ጋር በመጋጨቱ ነው ብለዋል።
የአደጋው መንስኤ በሁለቱም ተሽከርካሪዎች መሀከል የገባችውን አህያ ለማዳን ጥረት ሲያደርጉ ግጭቱ እንደተፈጠረ ተናግረዋል ።
በአደጋው የአይሱዙ ሾፌርና ረዳቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ በአውቶቢሱ ውስጥ በነበሩ ስድስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮማንደሩ ገልፀዋል ።
ከፍጥነት በላይ ማሽከርከርና የሌሊት ጉዞ ለአደጋው መፈጠር ሌላው ምክንያት መሆኑንም ከኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
በሌላ በኩል ደግሞ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በቦሌ ከተማ አካባቢ በአንድ ግለሰብ ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በድብቅ በበቆሎ ቡቃያ መሐል የለማው ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ ዕፅ መያዙን ኮማንደር አስቻለው አክለው ገልፀዋል።
አደንዛዥ ዕፁ ግለሰቦች ከአርሶ አደሩ መሬት በመኮናተር ሰሊጥ ነው በሚል ሽፋን እንደዘሩት ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል ።
አደንዛዥ ዕፁን የዘሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ለማቅረብ ፖሊስ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል ።
የወረዳው ልዩ ኃይል አባላት ፣ ፖሊስና ህብረተሰቡ በመተባበር አደንዛዥ ዕፁን እንዲወገድ አድርገዋል ።
ህብረተሰቡ ወንጀልን የሚያባብሱ ተግባራት ሲመለከት ፈጥኖ ለፀጥታ አካላት በመጠቆም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ኮማንደር አስቻለው መልእክት አስተላልፈዋል ።