ዩኒሴፍ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የህክምና ቁሳቁሰ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒሴፍ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የህክምና ቁሳቁሰ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15/2012 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚውል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቀሰ ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዴል ኮድር ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉን ዛሬ አስረክበዋል።
ድጋፉ ለህክና ባለሙያዎች የሚውል የፊት መሸፈኛ ጭንብል፣ የሙቀት መለኪያ መሣሪያና የህክምና አልባሳትን ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የህክምና ቁሳቁሶቹን ለየክልሎችና ተቋማት የሚያከፋፍል መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዴል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የህክምና ድጋፉ የተሰጠው በእንግሊዝ መንግሥትና በድርጅቱ ነው።
ድጋፉም የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ሌሎችም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ይህም የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ድርጅታቸው እንደሚሰራ ገጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍ ይህንን ብሔራዊ የቫይረሱን የምላሽ አቅም እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ከድጋፉ መካከል አንዳንዶቹ ቁሳቁሶች ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያሰችሉ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ ለክልሎች አንደሚሰራጭም ተናግረዋል።
ዩኒሴፍና የእንግሊዝ መንግሥት በጋራ ላደረጉት ድጋፍም ዶክተር ሊያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።