ቀጥታ፡

ለአገሪቱ መሪ የልማት ዕቅድ ዝግጅት በግብዓትነት የሚያገለግሉ ጥናቶች መጠናቀቃቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 ለአገሪቷ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታውቋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ33ኛው መደበኛ ስብሰባው የኮሚሽኑን የ11 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል። በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ሀገራችንን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የሚያስችልና በየአምስት ዓመቱ እየተመነዘረ ተግባራዊ የሚደረግ የማክሮ-ኢኮኖሚና የዘርፍ የልማት ግቦችን ከዘላቂ ልማት ግቦች በማገናዘብ ሀገራዊ መሪ የልማት ዕቅድ እየተተገበረ ይገኛል። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም እንደገለጹት፤ በማክሮ-ኢኮኖሚ፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በኢነርጂ መሰረተ ልማት፣ በሰው ኃብት ልማትና በትራንስፖርት መሰረተ ልማት/መንገድና ባቡር/ እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለመሪ የልማት ዕቅድ ዝግጅት ግብዓት የሚሆኑ የመነሻ ጥናቶች  በተያዘላቸው ዕቅድ ባለፉት 11 ወራት እንዲጠናቀቁ ተደርገዋል። ጥናቱ ረጅም የመሪ የልማት ዕቅድ ዝግጅት ልምድ ካለው የኮርያ የልማት ተቋም ጋር በመተባበር መዘጋጀቱንና በዚሁም የመሪ ዕቅዱን ይዘቶችና የዝግጅት ሂደቶች ያካተተ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በከተማ ልማትና ቤቶች እንዲሁም በስነ-ህዝብ ልማት ላይ ጥናቶችን ለማካሄድ የሥራ መዘርዝር በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩትና ከሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር ወደ ስራ መገባቱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። ለአብነትም በረጅም ጊዜ ምልከታ የአገሪቱን የውሃ ኃብት በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ያለውን ሚናና የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት የሚተነትንና የሚተነብይ/Haydro Economics Gap Analysis/  የተሰኘ ጥናት ከዓለም ባንክ የውሃ ኃብት ግሩፕ 2030 ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር የተሰራ የመነሻ ጥናት አስተያየት ተሰጥቶበት የመጀመሪያ ረቂቅ ሪፖርት በመዘጋጀት ላይ ይገኛልም ብለዋል። ይሁን እንጂ በከተማ ልማትና ቤቶች፣ በሥነ-ህዝብ ልማትና በዘላቂ ልማት ግቦች የፋይናንስ ፍላጎት ዙርያ የሚካሄዱ ጥናቶች በወቅቱ  ባለመጠናቀቃቸው የመሪ ዕቅዱን ዝግጅት መጀመር አልተቻለም ብለዋል። ባለፉት 11 ወራት የዘላቂ ልማት ግቦች የፋይናንስ ፍላጎትና ፋይናንሲንግ እስትራቴጂ ዙርያ የሚካሄዱ ጥናቶች 75 በመቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ 53 ነጥብ 3 በመቶ ተፈፃሚ መሆኑ በክፍተት ታይቷል። በመሆኑም በቀጣይ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን በማጠናከር ጥናቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁና የመሪ የልማት ዕቅድ ዝግጅት እንዲጀመርና ሂደቱ እንዲፋጠን የተደራጀና የተቀናጁ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም