ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝቦችን አንድነት እያጠናከረ ነው--ጎብኝዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝቦችን አንድነት እያጠናከረ ነው--ጎብኝዎች
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝቦችን አንድነት በማጠናከር ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጄንሲ ሰራተኞች ተናገሩ። ሰራተኞቹ ሰሞኑን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003ዓ.ም መሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠለት በኋላ በኢትዮጵያ ብሔሮቸ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ የአንድነትና አገራዊ ስሜት ተንጸባርቋል። ኢትዮጵያውያን ዳር እስከ ዳር አንድ የሚያደርጋቸው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ እድሜ፣ ጾታና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሳይለያቸው እየተጉ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ከግንባታው ሒደት ጀምሮ በጊዜ ፣ በገንዘብ፣ በሐሳብና በሞራል ድጋፍ ሁሉም የሚችለውን እያደረገ ነው። በዚህ የሕዝቦች ድጋፍ ግድቡ አሁን ላይ 66 በመቶ መጠናቀቁ መገለጹ ይታወሳል። የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጄንሲ ሰራተኞች እንደሚሉት "ግድቡ የጋራ አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክርና በአገሪቷ ሕዝቦች መካከል መቀራረብና መተሳሰብን እየፈጠረ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው"። የተሰማቸው የደስታ ስሜት በቃላት የሚገለጽ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ዳንኤል ግርማይ፤ ትልቋ ኢትዮጵያን በአንድ ማእከል ላይ አሰባስቦ ያስተያየንና ያገናኘን መድረክ ነው ብለዋል፡፡ ወይዘሪት ቤተልሄም ኤርዶሳ በበኩሏ ታሪካዊ ቦታ በመጎብኘቷ በጣም ደስተኛ እንደሆነች ገልጻ፤”ለትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ አንድነታችንን የሚያጠናክር፤ የቤተሰባዊነት ስሜት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው” ብላለች፡፡ “ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስር ከምንም በላይ እኛ ኢትዮጵያውያን መስራት እንደምችል የሚያሳስብ ነው” ያሉት ሌላው ጎብኝ አቶ ሀሰን ተገኘ ናቸው፡፡ የጉብኝቱ ተሳታፊ የየሆኑት አቶ ሀሰን ተገኘ ቀሪውን ስራ በአንድነት ጠንክረው በመስራት ከውጤቱ ተጠቃሚ በመሆን ሀገራችንን ከአደጉት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኤሌትሪክ ኃይልን በማመንጨት በዓለም ታላላቅ ከሚባሉ ግድቦች መካከል በ7ኛ ደረጃ የሚቀመጠው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ቀዳሚና በአንደኛነት ይጠቀሳል።