አርሂቡ ወሎ የበጎ አድራጎት ማህበር ለ115 ችግረኞች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አርሂቡ ወሎ የበጎ አድራጎት ማህበር ለ115 ችግረኞች ድጋፍ አደረገ
ደሴ/ ወልዲያ ሚያዚያ 14/2012 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ የሚገኘው "አርሂቡ ወሎ የበጎ አድራጎት ማህበር የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው 115 የድሃ ድሃ ወገኖች ለረመዳን ፆም የሚውል የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
በደሴ ከተማ የሚገኘው የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት ጣፈጠ ተስፋዬ እንደገለጸው ማህበሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ አቅመ ደካሞችን የመርዳት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፡፡
አቅመ ደካሞች የትንሳኤ በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁሞ አሁን ደግሞ የረመዳን ወር በመድረሱ አቅመ ደካሞች ያለ ችግር የሚጾሙበት የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግሯል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው የገቢ ምንጭ አማራጭ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች ሲሆን ከ60 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ዱቄት፣ ፓስታ፣ ዘይትና መሰል የምግብ እህሎች ተሰጥቶአቸዋል ።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ተጠቃሚ መካከል ወይዘሮ አይሻ ሁሴን እንደገለጹት ከዚህ በፊት የቀን ስራ እየሰሩ አምስት ቤተሰቦቻቻውን ያስተዳድሩ እንደነበረ አስታውሰው ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ ስራ በማቆማቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
በማህበሩ የተደረገላቸው ድጋፍም ፆሙን ተረጋግተው ለመፆም እንደሚያግዛቸው በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል ።
አቶ አስቻለው ቦጋለ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በጤና ማጣት ምክንያት ከቤት በመዋላቸው በረመዳን ጾም እቸገራለሁ የሚል ስጋት እንደነበረባቸው ጠቅሰው በተደረገላቸው ድጋፍ ጊዚያዊ ችግራቸውን በመፈታቱ እንደተደሰቱ ገልፀዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይልማ ተረፈ በበኩላቸው በኮሮና ምክንያት በአቅመ ደካሞች ላይ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ከማህበሩ ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው ብለዋል ።
ከተማ አስተዳደሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለአቅመ ደካሞች የሚሆን 6 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በምግብ እህል በማሰባሰብ አቅም ለሌላቸውሰዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።
ሃብት የማሰባሰቡ ስራ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉ የምግብ እህሎች በስፋት እየተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በወልዲያ ከተማ አስተዳደር በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ከሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማሰባሰብ ችግረኞችን የመርዳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል የግብዓት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተገኘ ፈንታው ገልፅውል ።
እስከ አሁን ድረስ ከተሰበሰበው ሃብት አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ለ2 ሺህ 200 አቅመ ደካሞች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ።