ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ስራ አሁንም ከፍተኛ ትኩረትን ይሻል- የአፋር ክልል ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 14/2012 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ስራ በትኩረትና ቀጣይነት ባለው መልኩ መከናወን እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የአፋር ክልል ከኤርትራና ጅቡቲ ጋር አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ በተለይ በጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ በየእለቱ ከፍተኛ የሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ ይታያል።

በመሆኑም በተለይ በጅቡቲ እየተስፋፋ የመጣው የኮሮናቫይረስ ለክልሉ ብሎም አጠቃላይ ለኢትዮጰያ የቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚሻው ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በክልሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ከተጀመረ ቆየት ቢልም በሚፈለግው ልክ የባህሪ ለውጥ እየታየ ዓለመሆኑንም ይናገራሉ።

በአሳኢታ ወረዳ አካባቢው በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ያገኘናት ወጣት ኤርጎ አበበ ነዋሪዎች የኮሮናቫይረስን እንዲከላከሉ በማስተማር የድርሻዋን በመወጣት ላይ መሆኗን ትናገራለች።

ሆኖም በዚህ በጎ ምግባር ስራዋ እንደታዘበችው በርካቶች ስለቫይረሱ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ግደለኝነት ይታይባቸዋል ብላለች።

የድንበር አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄ ማድርግ እየተገባ በስፋት መዘናጋት እየተስተዋለ መሆኑን ገልፃለች።

የአፋር ክልል የጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ በበኩላቸው በክልሉ የኮሮናቫይረስ እንዳይስፋፋ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም እስከ ሚያዝያ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ብቻ ወደ ክልሉ በሚገቡና በሚወጡ ከ260 ሺህ በላይ ሰዎች የሙቀት ልኬት ፍተሻ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የመከላከልና የግንዛቤ ማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደተደነገገው በድንበር አካባቢ ከፍሳሽና ደረቅ ጭነት አገልግሎት ውጭ የሰዎችን እንቅስቃሴ ይከለክላል።

የኢዜአ ሪፖርተር እንዳረጋገጠው ከሆነ ግን እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በጅቡቲና ኤርትራ ድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች አሉ።

መረጃዎች እነደሚያመለክቱት ኤርትራ እስካሁን 39 ዜጎቿ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን ሞት ግን አላስመዘገበችም።

ጅቡቲ ደግሞ 945 ዜጎቿ ቫይረሱ ሲገኝባቸው የሁለት ሰዎች ሞት መኖሩንም አስመዝግባለች።

ይህም በመሆኑ ከጅቡቲና ኤርትራ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎችን በለይቶ ማቆያ ክትትል ለማድረግ እንዲቻል የፌዴራሉን መንግስት ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

የአፋር ህዝብ ለዘመናት የዘለቀውን የ"ዳጉ" ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመጠቀም የተለያዩ ችግሮችን እንደሚያልፍ ሁሉ የኮሮናቫይረስንም ሊዋጋ እንደሚገባ ዶክተር ፈረጅ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን 9 ሺህ 771 ሰዎች ላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 116 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም