በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋጁን ተላልፈው የተገኙ 105 አሸከርካሪዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋጁን ተላልፈው የተገኙ 105 አሸከርካሪዎች ተቀጡ
አሶሳ ፣ ሚያዚያ 14 / 2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው የተገኙ 105 አሸከርካሪዎች መቀጣታቸውን የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል አብይ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የግብረ ኃይሉ የጸጥታ ዘርፍ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ እንደገለጹት አዋጁን ተላልፈው የተገኙት የባጃጅ ፣ ህዝብ ማመላለሻ እና ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ናቸው።
ቅጣቱ የተላለፈባቸው 29 የህዝብ ማመላለሻ፣ 51 የባጃጅ እና 25 የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች መሆናቸውን አቶ አብዱላዚዝ አመልክተዋል።
አሽከርካሪዎቹ አዋጁን ተላልፈው ከተፈቀደላቸው ተሳፋሪ በላይ መጫናቸው ተደርሶበት እያንዳንዳቸው እስከ 300 ብር ገንዘብ እና በመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተቀጡ አስታውቀዋል፡፡
በተለይም የህዝብ ማመላለሻዎች ኬላዎችን አልፈው ትርፍ እንደሚጭኑ ያመለከቱት አቶ አብዱላዚዝ በትርፍነት ለመጫን በእግር ከከተሞች ውጪ ተጉዘው የሚጠብቁ ጥቂት ህገ-ወጥ ግልሰቦች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በአዋጅ ገደብ የተጣለበት ለራሱ ደህንነት መሆኑን ተረድቶ በትርፍነት ከመሳፈር በመቆጠብ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡