በማጃንግ ዞን አደረጃጀቶችን በመፍጠር ኮሮናን ለመከላከል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማጃንግ ዞን አደረጃጀቶችን በመፍጠር ኮሮናን ለመከላከል እየተሰራ ነው
ጋምቤላ ፣ ሚያዚያ 14/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አስታወቁ።
ምክትል አስተዳደሪው አቶ እስማይል ገለታ ለኢዜአ እንደገለጹት አደረጃጀቶቹ በግብረ ኃይል የተሳባሰቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚገኙበት ከዞን እስከ ቀበሌ የዘለቀ ነው።
በተለይም የገጠሩ ማህበረሰብ አካላዊ ርቀቱን እና ንጽህናውን በመጠበቅ በሽታውን መከለከል እንዲችል የተደራጁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶችን በመጠቀም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ወጣቶቹ ግንዛቤን ከመፍጠር ባለፈ ተሽከርካሪ በሚያልፉባቸው ቀበሌዎች ኬላ በማቋቋም እጅ የማስታጠብና ከመጠን በላይ በሚጭኑ አሽከርካሪዎችን የመቆጣጠር ሥራ እያካሄዱ ነው "ብለዋል።
ቫይረሱ ቢከሰት ሊፈጠር የሚችለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን የምግብ እህልና ሌሎች የሃብት የማሰበሳብ ተግባር እስከ ገጠር ቀበሌዎች እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዞኑ በልግ አብቃይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ በበሽታው ስጋት እንዳይዘናጋም በየደረጃው በተቋቋሙ ግብር ኃይሎች አማካኝነት የንቅናቄ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በዞኑ መንጌሽ ወረዳ የሾኔ ቀበሌ በበጎ ፈቃድ ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል ምትኩ ደጀኔ በሰጠው አስተያየት ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው እንዲጠበቅ ቤት ለቤት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እያካሄዱ መሆኑን ገልጿል።
ወጣቱ እንዳሉት በተለይም አርሶ አደሩ ወደ እርሻ ስራው ሲሄድም ሆነ ሲመለስ እጁን በማሳሙና እንዲታጠብ በመቀስቀስ እያስተማሩ ነው።
በቀበሌያቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ስለበሽታው አስከፊነትና መከላከያው መንገድ ትምህርት እየሰጧቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ባሳዝን ጌታቸው ናቸው።
የሚሰጣቸውን ትምህርት መሰረት አድርገው እራሳቸውን ከበሽታው በመጠበቅ የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገለጸዋል።