ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ የኮሮና ሻይረስን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የ52 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አሰባሰበ

ኢዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2012(ኢዜአ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የኮሮና ሻይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከ52 ሚሊዩን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰቡን አስታወቀ።

ድጋፉ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተሰባሰበው ''በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል'' በኩል በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ነው።

ሚኒስቴሩ  ድጋፉን ያሰባሰበው ዓለም አቀፍ  ስጋት የሆነውን ቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወሰደው ተነሳሽነት መሆኑም ተመልክቷል።

ኩባንያዎቹ በአገርና በክልሎች በተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴዎች በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች 37ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ያደረጉ ሲሆን፣ቀሪው ድጋፍ በዓይነት እንደተከናወነ ተገልጿል።

በዓይነት በተደረገ ድጋፍ ደግሞ ህንጻዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የእጅ ጓንቶችና የአፍ ጭምብሎች ይገኙበታል።

የኮቪድ 19 ብሔራዊ ድጋፍ አሰበሰብ ኮሚቴ የሀብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት ሚኒስቴሩ የኮቪድ 19ን ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገው ላለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  

ማህበረሰቡ ወረርሽኙ አገር ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ለመቀነስ መተባበርና ከመንግስት ጎን መቆም ይገባል ብለዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው ኩባንያዎቹ አገር አቀፍ ጥሪውን ተቀብለው ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፣ ሌሎችም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

ከድጋፉ ኩባንያዎቹ በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦችን በገንዘብ 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በዓይነት ደግሞ 13 ሚሊዮን ብር የሚገመተው እንደሚሰራጭ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም