በክልሉ ኮሮናን በመከላከል ረገድ የሚስተዋለው መዘናጋት ሊስተካከል ይገባል--አቶ አሻድሊ ሃሰን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኮሮናን በመከላከል ረገድ የሚስተዋለው መዘናጋት ሊስተካከል ይገባል--አቶ አሻድሊ ሃሰን
አሶሳ ፣ ሚያዚያ 14 / 2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከሉ ረገድ በግብረ ኃይሉም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት በአስቸኳይ ሊስተካከል እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አሳሰቡ፡፡
የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል አብይ ግብረ ኃይል በእንቅስቃሴዎቹ ዙሪያ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ እና ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ቫይረሱ ስለሚያስከትለው ጉዳት ፣መተላለፊያውና መከላከያው መንገዶች በክልሉ በየደረጃው ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡
"ይህም መጨባጥን አስቀርቷል" ብለዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልገውን በጀት በማሰባሰብ ረገድም ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አውስተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተላለፉ ላይም ተመጣጣኝ የገንዘብ እና የማስጠንቀቂያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
"ይሁንና በአብይ ግብረኃይሉም ሆነ በተዋረድ በሚገኙ አደረጃጀቶች አባላት ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት አለ" ብለዋል።
በተለይም በመተከል ዞን በውስን ወረዳዎች ገቢን ለማሰባሰብ ከተደረገው ጥረት ውጪ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለመለወጥ የተሰሩ ተግባራት ውስን እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በከተሞች በበጎ ፈቃደና ወጣቶች ጭምር በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ቢመጣም በተለይም የገጠሩ ህብረተሰብ አሁንም አካላዊ ርቀቱን ሳይጠብቅ የተለመደውን ግንኙነት መቀጠሉ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የድንበር አካባቢ ህገ-ወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ሊቆም አለመቻሉንም ሌላው ስጋት ነው ብለዋል።
ቫይረሱ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ባልታወቀበት በአሁኑ ወቅት በማህበረሰቡም ሆነ በየደረጃው በሚገኙ ግብረ ኃይል አባላት የሚስተዋለው መዘናጋት በአስቸኳይ ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አቶ አሻድሊ "አመራሮቹ ለስራው ወሳኝ የሆኑ አካላት እንዲካተቱ የግብረ ኃይላቸውን አደረጃጀት እንደገና እስከማዋቀር የደረሰ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡
በገቢ አሰባሰብ ረገድም እስከ አርሶ አደሩ በመውረድና ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገቡ አካላትም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርጉ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በተለይ በድንበር አካባቢ ያለውን ሥራ በትኩረት ሊያከናውኑ እንደሚገባ ጠቁመው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የሸቀጣሸቀጥ እጥረት እንዳለ ለማስመሰል የሚጥሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ እንዲጠናከር አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በተለይ ግብረ ኃይሉ ህብረተሰቡን ከቫይረሱ ለመታደግ መስዋዕትነት መክፈል የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንዳለ በመረዳት ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡