በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ስጭርትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ስጭርትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሐረር ፣ ሚያዚያ 14 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሶማሊያ ህዝቦችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በድንበር አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴ ለመግታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በድንበር አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተካሄዱ ባሉት ስራዎች ዙሪያ የጸጥታና የሚመለከታቸው አካላት በቶጎ ውጫሌ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ እንተናገሩት የኢትዮዽያና የሶማሌ ላንድ ህዝቦች ለበርካታ ዓመታት በአንድነት የኖሩ ወንድማማቾች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱን ህዝቦች ከኮሮና በሽታ ለመጠበቅ በአካባቢው የሰዎችን እንቅስቃሴ እንዲገታ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሽታውን ለመከላከል የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ድንበር ከማቋረጥ እንዲቆጠቡ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም "አልፎ አልፎ ድንበር እየተጣሰ ዜጎች ወደ ሁለቱም ሀገራት የመዝለቅ ሁኔታ እየታየ ይገኛል" ብለዋል።
ይህም ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር በሁለቱም ወገን የሚገኙ የጸጥታ አካላት፣የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣የጉምሩክ ኃላፊዎች፣የኢሚግሬሽንና ደህነነት ሰራተኞች ችግሩን በጋራ መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ድንበሩ የተዘጋው የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች እየተስፋፋ ከመጣው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መሆኑንና ወንድማማችነታቸው ግን ለዘላለም እንደሚቀጥል ግንዛቤ የመስጠት ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የሶማሌ ላንድ መከላከያ ኢታማጆር ሹም ሜጀር ጀነራል ኖህ ኡስማኢል በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ በተለይ ባደጉት ሀገራት ላይ ያስከተለው ጉደት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የኢትዮዽያ መንግስትም ቫይረሱን ለመከላከል እያከናወነው የሚገኘው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በድንበር በኩል የሚስተዋለው የሰዎች ዝውውር ለመግታት መንግስት ያወጣውን ህግ ህዝቡ ማክበር እንዳለበትም አመልክተዋል።
የሶማሌ ላንድም ከጅቡቲና ኢትዮዽያ ጋር የሚያዋስኑ ድንበሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ዜጎች ባሉበት እንዲቆዩ ለማስቻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሶማሌ ክልል የቶጎ ጫሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙክታር ሀቢብ ናቸው።
በግብረ ኃይሉ አማካኝነት ህብረተሰቡ ስለቫይረሱ ያለውን ግንዛቤ ለማደበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከንቲባው እንዳሉት በአሁኑ ወቅትም ቫይረሱን ለመከላከል ከሶማሌ ላንድ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ከፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ሰዎች በያሉበት እንዲቆዩ እየተደረገ ነው።
በተለይ ድንበሩ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዋናው መንገድ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሰዎች ዝውውር እንዳይኖር የጥበቃ ስራ ማጠናከራቸውን ተናግረዋል።
የምስራቅ ዕዝ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ኮረኔል መንገሻ ፈንታው በበኩላቸው በቀጠናው የሚገኙ የጸጥታ አካላት ቫይረሱን ለመከላከል ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በመሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ለማስከበር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"የተፈቀዱትን ለማስፈጸም ደግሞ ከኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ጋር በመነጋገር እየሰራን ነው " ብለዋል።
በተለይ ከሶማሌ ላንድ ባለፈ ከጅቡቲ የጸጥታ እና አመራር አካላት ጋር የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በድንበር አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በውይይቱ የሶማሌ ላንድና የምስራቅ ዕዝ የመከላከያ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች፣የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባላት ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ የተዘጋውን የቶጎ ውጫሌ ድንበርና ሌሎች ቫይረሱን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል።