የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ፍላጎትን ለመመለስ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ፍላጎትን ለመመለስ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ያመጣውን የአየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ፍላጎትን ለመመለስ እየሰራች እንደምትገኝ ተገለፀ ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በርካታ የጭነት አገልግሎትና የህክምና ቁሳቁስ በሚፈለጉበት ቦታ ማድረስን የመሳሰሉ አስፈላጊ የጭነት ፍሰት የማመቻቸት ስራ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
በአፍሪካ በትልቁ የትራንስፖርት ጭነት ተርሚናል ስር ያለው ዘመናዊው የኢትዮጵያ የጭነት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የፋርማሲ ክንፍ በአፍሪካና በሌሎች አገሮች የህክምና ቁሳቁሶች መላኪያ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው።
የፋርማሲ ክንፉ ባለው የሙቀት መቆጣጠሪያ ስርዓት በተለያዩ የሙቀት ክልሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ለመያዝ የሚያስችል መሆኑም ተብራርቷል።
ስራውን ለመከወን የተለዩና የሰለጠኑ ባለሙያዎች በዓለም አየር መንገድ ትራንስፖርት ማህበር ህግና መመሪያዎች እና ሌሎች በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ባሉ ተቆጣጣሪ አካላት አሰራር መሰረት ይከወናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የኢትዮጵያ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሚናና አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የህይወት አድን የህክምና አቅርቦትን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማጓጓዝ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ጥረት ላይ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።