ቀጥታ፡

ለኮድ ሁለት መኪኖች የወጣው ፈረቃ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችንና የአምቡላንሶችን ምልልስ ለማፍጠን የታሰበ ነው-ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2012 (ኢዜአ) ኮድ ሁለት መኪኖች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉ የኮቪድ - 19 ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን የሕዝብ ማመላለሻና የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎችን ምልልስ ለማፋጠን መሆኑን የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት መንግስት የሚያወጣቸው መምሪያዎች ሕዝቡን ከአደጋ ለመታደግ መሆኑ ታውቆ ለተፈጻሚነቱ ተባባሪ መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመግታት በትራንስፖርት ዘርፉ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ መንግስት ስርጭቱን ለመግታት ያግዘው ዘንድ በኮድ ሁለት የተመዘገቡ የግል መኪኖች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ ተወስኖ ወደትግበራ ተገብቷል።

በዚሁ መሰረት ጎዶሎ ቁጥር ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ለሙሉ ቁጥር ዜሮን ጨምሮ ማክሰኛ፣ ሐሙስና ቅዳሜ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዷል፤ አሁድ ለሁሉም መፈቀዱ የሚታወስ ነው።

ውሳኔው ከሚያዚያ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተፈጸመ ቢሆንም የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች "ሂደቱ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ላይ ጭንቅንቅ ፍጥሮ ለቫይረሱ የሰዎችን ተጋላጭነት ይጨምራል" የሚል ስጋት እየሰነዘሩ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለኢዜአ የሰጡት የትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ "ውሳኔ በአግባቡ የታሰበበት ነው" ይላሉ።

"ከአገሪቷ 53 በመቶ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱት በአዲስ አበባ ሲሆን የኮድ ሁለት የትራንስፖርት አገልግሎት ድርሻም ከ8 በመቶ አይበልጥም" ሲሉም ይገልጻሉ።

በቁጥር ከ15 ሺህ የማይበልጡት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ግን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ ነው ያመለከቱት።

እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ በአዲስ አበባ 208 ሺህ ኮድ ሁለት መኪኖች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከአሽከርካሪው ውጭ እንዲጭኑ የሚፈቀደው በአማካይ ከሁለት ሰው አይበልጥም።

መንግስት በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ ይህን መመሪያ የማውጣት ደረጃ ላይ የደረሰው ሌሎች የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅማቸው በግማሽ በመቀነሱ ምልልሳቸውን በመጨመር በቂ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላው መመሪያ እንዲተገበር የተፈለገበት ምክንያት አምቡላስን ጨምሮ በሽታውን ለመከላከል ለሚደረጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች መንገዶችን ክፍት ለማድረግ ታስቦ ነው።

"ከዚህ በተጨማሪ የመድኃኒት፣ የምግብና የሌሎች አስፋለጊ ግብዓቶች ጉዞም በከተማዋ ውስጥ በነጻነት እንዲደረግ ለማስቸልም ጭምር ነው" ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

መንግስት ሰዎች በተወሰነ መልኩ ቤታቸው እንዲቀመጡ በመከረው መሰረት በሳምንት ቢያንስ ለሦስት ቀናት ከቤታቸው ሆኖው እንዲሰሩና አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድተዋል።

አቶ ምትኩ እንዳሉት ባለስልጣኑ በዋናነት ዋና ዋና መንገዶች ላይ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በመፍታት የሰዎችን ተጋላጭነት መቀንስ ይቻላል የሚል ዕምነት አለው።

ሕዝቡ ይህንኑ እውነታ በመረዳት መንግስት የሚያወጣቸው መመሪያዎች ለሕዝቡ ደህንነት በማሰብ መሆኑን ተረድቶ ለተፈጻሚነቱ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ ቀርበዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ እስካሁን ከተላለፉት ውሳኔዎች መካከል የሕዝብ ማመለሻ ተሽክርካሪዎች በግማሽ አቅም አገልግሎት እንዲሰጡና ኮድ ሁለት መኪኖች በፈረቃ እንዲሰሩ ተደርጓል።

የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች በግማሽ አቅም ከመጫን ጎን ለጎን አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እንዲሰሩም መደረጉ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም