ቀጥታ፡

በግንባታ ቦታዎች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ መመሪያ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤  ሚያዝያ 13/2012 (ኢዜአ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በግንባታ ቦታዎች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንዲያግዝ ያወጣውን አስገዳጅ መመሪያ ይፋ አደረገ። 

ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ መመሪያውን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የከሮናቫይረስ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመከላከል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የግንባታ ዘርፉም ግዙፍ ሀብት የሚንቀሳቀስበት እንደመሆኑ የከፋ ተጽዕኖ እንዳይመጣ ተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አቅጣጫ መቀመጡም የሚታውስ ነው።

ኢንጂነር አይሻ እንደተናገሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወደ መሬት ለማውረድ ከግንባታ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ጋር በመሆን አስገዳጅ መመሪያ ተዘጋጅቷል።

"መመሪያው ከኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር፣ ከኢትዮጵያ መሀንዲሶች ማህበር፣ ግንባታ ተቆጣጣሪዎች፣ አማካሪ ማህበራትና ሌሎችም ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበር ይሆናል " ነው ያሉት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በግንባታ ቦታዎች ላይ የሠራተኞች ጤንነትን እየተከታተለ ለሥራ ተቋራጩ ሪፖርት የሚያደርግ ባለሙያ መመደብ ግዴታ ነው።

"ከዚህ ባለፈም በሠራተኛ መውጫና መግቢያ ሰዓት ለሠራተኞች ስለበሽታው ግንዛቤ መስጠት የግድ ይላል" ያሉት ኢንጂነር አይሻ፣ ከሠራተኞች በስተቀር ከውጭ ወደ ግንባታ ቦታዎች የሚገባ ሰው መኖር እንደሌለበትና የሚገባ ሰው ካለም የጤናው ሁኔታ ተረጋግጦ መሆን እንዳለበት በበመሪያው ላይ መቀመጡን አስረድተዋል።

የሥራ ተቋራጭ የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በሟማላት ለሠራተኞች በቀን ሁለት ጊዜ ሙቀታቸውን መለካት እንዳለበት ጠቁመው፣ ሙቀቱ ከፍ ያለ ሠራተኛ ካለ ለጤና ባለሙያዎች ሪፖርት ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።

"የሙቀት መጠናቸው ከ37 ነጥብ 2 በላይ የሆኑ ሠራተኞች ወደ ጤና ተቋም ሂደው ክትትል እንዲደረግላቸው በመመሪያው ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል" ብለዋል።

በግንባታ ቦታዎች ላይ ውሃ፣ ሳሙና፣ የእጅ ጓንትና ሳኒታይዘር የመሳሰሉ ንጽህና መጠበቂያ ግበአቶችን ማሟላት የመመሪያው ሌላው አካል እንደሆነም ኢንጂነር አይሻ ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ የራሱን ትራንስፖት ማቅረብ፣ በግንባታ አቅርቦት ርክክብ ወቅት ጥንቃቄ ማድረግና ጥሬ እቃው ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በጸረ ተባይ ኬሚካል ማጽዳት ተገቢ ነው።

የሥራ ተቋራጮች የሠራተኛን ጥግግት ለመቀነስ በፈረቃ ማሰራትና መመሪያዎች መተግበራቸውን  በክትትል ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አመሃ ስሜ በበኩላቸው "ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፉ ያለው ተጽዕኖ እስካሁን ባይለይም የዋጋ ንረትና የግንባታ መዘግየት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት ይቻላል" ሲሉም አብራርተዋል።

ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አንስተው፣ በሥራ ተቋራጮች ላይ ጫና ቢፈጥርም ሠራተኞች ህይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ወደ ግንባታ ቦታዎች የሚመጡበት ዕድል መኖሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም