የረመዳን ጾም ሀሙስ ወይም አርብ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የረመዳን ጾም ሀሙስ ወይም አርብ ይጀመራል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2012 (ኢዜአ) የዘንድሮው ረመዳን ጾም ሀሙስ ወይም አርብ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የዘንድሮው የረመዳን ጾም እሮብ ምሽት ጨረቃ ከታየች ሀሙስ ካልታየች ደግሞ አርብ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስረድቷል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ የ1 ሺህ 440ኛውን የረመዳን ጾም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም እሮብ ጨረቃ ከታየች ፆሙ ሀሙስ የሚጀመር ሲሆን በእለቱ ካልታየች ደግሞ አርብ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ከፆም በተጓዳኝ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከጠቅላይ ምክር ቤቱ እና ከመንግስት የሚሰጠውን መግለጫ በመቀበል ተግባራዊ ማድርግ እንዳለበትም ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር አሳስበዋል።
የኮሮና ወረርሽን መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስም ሙስሊሙ የረመዳን ተግባራትን (ኢባዳዎችን) በቤቱ ሆኖ ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ረመዳን የምህረት ወር መሆኑን በመረዳት ፀሎትን ማጠናከር ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተለይ አቅመ ደካሞችንና ችግረኞችን መርዳትም ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑን መክረዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት አደጋውን ለመከላከል እያደረገ ላለው ጥረትም ህዝበ ሙስሊሙ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የኮሮና ወረርሽን መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ በዚህ ረመዳን በቤት ውስጥ ጀመኣ በመፍጠር ከቤተሰብ ጋር መስገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህ ችግር እንኪወገድ ከቤተሰብ ውጭ በጉርብትናም ቢሆን ተሰባስቦ መስገድ እንደማይቻል የተናገሩት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ መንግስት ከአራት ሰው በላይ ሊሰባሰብ እንደማይገባ ያሳለፈውን አዋጅ ማክበር ያስፍልጋል ብለዋል።
የመስጊድ ኢማሞች በድምፅ ማጉያዎች ለህብረተሰቡ ትምህርት የሚሰጡበት መንገድ እንዲመቻች መደረጉንም ተናግረዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በቤቱ እያደረገ ያለውን ዱኣ እና ፀሎት በረመዳንም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ በማቅረብ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስትላልፈዋል።