ድንበር አቋርጠው የገቡ 65 ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ድንበር አቋርጠው የገቡ 65 ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ተደረገ
አሶሳ (ኢዜአ)ሚያዚያ 13 / 2012፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ 65 ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ መደረጉን የክልሉ የቫይረሱ መከላከል ንዑስ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
በግብረ ኃይሉ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን አባል አቶ መለሰ በየነ ለኢዜአ እንደተናገሩት በሽታውን ለመከላከል ክልሉ ከሱዳን ጋር የሚዋሰንበት ስድስት የጠረፍ በሮች እንዲዘጉ ተደርጓል።
ወደ ማቆያ የገቡት ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ በጫካ ውስጥ ድንበር አቋርጠው በሸርቆሌ እና ኩርሙክ የጠረፍ ከተሞች በኩል የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በጠረፍ በሮቹ ባደረጉት ጠብቅ ቁጥጥር የተገኙት እነዚህ ሰዎች ትናንት እና ዛሬ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተዘጋጀው ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ አብይ ግብረ ኃይሉ የጤና ዘርፍ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው ከሰዎቹ መካከል መካከል16 በህገወጥ መንገድ የገቡ ሱዳናዊያን እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ቀሪዎቹ 49 ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር ወጥተው በተመሳሳይ ተመልሰው ለመግባት ሲሞክሩ የተገኙ ኢትዮጵያዊን ናቸው ብለዋል።
ከግለሰቦቹ የአክታ ናሙና እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመው ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ ነገ ወደ አዲስ አበባ እንደሚላክም አመልክተዋል፡፡
ናሙናዎች የማሰባሰብ ሥራ በዩኒቨርሲቲው ለይቶ ማቆያ በተመደቡ የጤና ባለሙያዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ግልሰቦቹ የተገኙት በህብረተሰቡ ጥቆማ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የአብይ ግብረ ኃይሉ አባል እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሃመድ ሃምደኒል ናቸው።
በክልሉ ድንበር አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ የበሽታው መከላከያ መንገዶችን በመተግበር መሠል ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መረጃ በመስጠት ሳይዘናጋ ራሱን እንዲጠብቅም የግብረ ኃይሉ አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡