ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መላምቶች

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ19) በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ውሃን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ስርጭቱ እየሰፋ መጥቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

ኮቪድ-19ን አስመልክቶ በዓለም ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሰዎች እስከ ሴራ ንድፈ ሀሳብ የዘለቁ የሃሰት መረጋዎችን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ምክር ለዜጎች በሚል በዓለም ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ ያሉ የተሳሳቱ መላ ምቶችን  በመለየት ህዝብ እንዲያውቃቸው በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

የመጀመሪያው መላምት የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትወርክ ቫይረሱን ያስተላልፋል የሚል ነው። ይህም የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ድርጅቱ አስገንዝቧል።

ቫይረሶች በሬዲዮ ሞገዶች /በሞባይል ኔትወርኮች ውስጥ እንደማይጓዙ የገለጸው ድርጅቱ፤ ኮቪድ-19 የ5-ጂ የሞባይል ኔትወርክ በሌለባቸው አገሮችም በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን ገልጿል።

ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲያስነጥሱ፣ ሲያስሉና ሲያወሩ በሚወጣ ፈሳሽ ነገር (ድሮፕሌትስ) የኮሮናቫይረስ ይተላለፋል።

በተጨማሪም ሰዎች የተበከሉ ቦታዎችን ከነኩ በኋላ አይናቸውን፣ አፍንጫቸውንና አፋቸውን ከነኩ በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ።

አዲስ አበባ ሚያዚያ 12/2012(ኢዜአ)ከ25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሚገኝ ሞቃታማ አካባቢዎች መቆየትና ጸሐይ መሞቅ የኮሮናቫይረስን ይከላከለዋል የሚለው ድግሞ ሌላኛው መላምት ነው።

አንድ ሰው በየትኛውም ሞቃታማና ጸሐያማ የአየር ንብረት ውስጥ ቢሆን የኮሮናቫይረስ እንደሚያዝና ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው አገራትም የኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በየጊዜው በሚያወጧቸው ሪፖርት እያደረጉ ይገኛል።

ሌላኛው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያለው መላምት ኮቪድ-19 የሚተላለፈው ሞቃታማ እና እርጥበት አዘል በሆኑ አካባቢዎች ብቻ እንደሆነና ቀዝቃዛ አየርና በረዶ ቫይረሱን ይገላል የሚል ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ-19 በሁሉም ቦታዎች የሚተላለፍ የአየር ንብረት ሁኔታን የማይለይ እንደሆነ ገልጿል።

ቀዝቃዛ አየርና በረዶ ኮሮናቫይረስን ሆነ ሌሎች ቫይረሶችን እንደማይገልና አንድ ሰው በየትኛውም የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ ቢገኝ አማካይ የሰውነት ሙቀት መጠኑ ከ36 ነጥብ 5 እስከ 37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ባለው መጠን ውስጥ እንደሚቆይም አመልክቷል።

ከሙቀት ጋር ተያይዞ ያለው ሌላኛው መላ ምት በሞቀ ውሃ ገላን መታጠብ ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የሚል ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት በሞቀ ውሃ ገላን መታጠብ ከኮሮናቫይረስ እንደማያድንና አንድ ሰው በየትኛውም የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ ቢገኝ አማካይ የሰውነት ሙቀት መጠኑ ከ36 ነጥብ 5 እስከ 37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ባለው መጠን ውስጥ እንደሚቆይም ገልጿል።

በጣም በሞቀ ውሃ ገላን መታጠብ ቆዳን በማቃጠል ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አስታውቋል።

ዜጎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ እጃቸውን ቶሎ ቶሎ በውሃና በሳሙና መታጠብ እና አይን፣ አፍንጫና አፋቸውን አለመንካት እንደሚገባቸው የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

ሌላኛው መላምት አንድ በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ቫይረሱ እድሜ ልክ ከዛ ጋር ይቆያል የሚለው ነው።

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከቫይረሱ ማገገምና ቫይረሱን ከሰውነታቸው ማስወገድ እንደሚችሉ የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

አንድ ሰው በአተነፋፋሱ ላይ እክል ከገጠመው፣ ጉንፋን ከያዘውና ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት ካለው ወደ ጤና ተቋም ስልክ መደወልና በአቅራቢው ወደ ሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት ገልጿል።

አንድ ሰው ሳያስነጠስ ወይም የምቾች ማጣት ስሜት ሳይሰማው ትንፋሽን ለ10 ሰከንድ እና ከዚያ በላይ አምቆ ያዘ ማለት ከኮሮናቫይረስ ነጻ ነው የሚለው ሀሳብ ሰዎች ያስቀመጡት ሌላኛው መላምት ነው።

አንድ ሰው ሳያስነጠስ ወይም የምቾች ማጣት ስሜት ሳይሰማው ትንፋሽን ለ10 ሰከንድ እና ከዚያ በላይ አምቆ ያዘ ማለት በኮሮናቫይረስ ተጠቂ ሊሆን አይችልም የሚለውን ነገር የሚያሳይ አይደለም ይላል የጤና ድርጅቱ።

ደረቅ ሳል፣ ከፍተኛ የድካም ስሜትና ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት ከኮሮናቫይረስ ምልክቶች መካከ የሚጠቀሱ እንደሆኑና አንዳንድ ሰዎች የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ጨምሮ ከባድ የበሽታው ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ።

አንድ ሰው በቫይረሱ መያዝ አለመያዙን ትንፋሽን በማመቅ ማወቅ እንደማይቻልና ይህንን ማድረግም ለአደጋ እንደሚያጋልጥ የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ መያዝ አለመያዙን ማረጋገጥ የሚችለበት ትክክለኛ አማራጭ የላብራቶሪ ምርምራ ብቻ እንደሆነም ተመልክቷል።

ሌላኛው መላምት አልኮል የኮሮናቫይረስን ይከላከላል የሚል ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅት ይሄን ሀሳብ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ገልጿል።

በፍጥነት ከተገቢው መጠን በላይ አልኮል መጠቀም የጤና ችግሮችን ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑን አመልክቷል።

የወባ ትንኝ ንክሻ የኮሮናቫይረስን ያስተላለፋል የሚል መላምት ሰዎች ያስቀምጣሉ።

እስካሁን ባለው ሁኔታ በወባ ትንኝ መነከስ እና የወባ ትንኝ ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ ምንም አይነት ማረጋገጫ እንዳልተገኘ የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

ሌላኛው መላምት የታጠበ እጅ ማድረቂያ ሙቀት አመንጭ ማሽን (ሀንድ ድራየርስ) የኮሮናቫይረስን ይገድላል የሚል ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት "አረጋግጫለሁ" እንዳለው ግን እጅ ማድረቂያ ሙቀት አመንጭ ማሽኖች በፍጹም ቫይረሱን እንደማይገድሉ ገልጿል።

ይልቁንም ከቫይረሱ ራስን ለመጠበቅ መንገዶች እጅን አዘውትሮ በውሃና በሳሙና መታጠብ እንዲሁም እጅን በአልኮል አልኮል ነክ ፈሳሾች ማጽዳት አንደሆነ አስታውቋል።

አንድ ሰው እጁን ከታጠበ በኋላ በሶፍትና በሞቀ አየር አመንጭ ማሽን (hot air dryer) እጁን ማድረቅ እንደሚችል ነው ድርጅቱ የገለጸው።

ልዕለ ሀምራዊ ጨረርን (ultraviolet radiation) ተጠቅመው ለማድረቅ እርጥበት ያላቸውን ነገሮች የሚያደርቁ መሳሪያዎች የኮሮናቫይረስን ይገድላሉ የሚለው መላምት ሰዎች ያስቀምጣሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት ለዚኛው መላምት የሰጠው ምላሽ ልዕለ ሀምራዊ ጨረር የሚጠቀሙ መሳሪያዎችም በጭራሽ ቫይረሱን የመግደል አቅም የላቸውም።

ልዕለ ሀምራዊ ጨረርን የሚጠቀሙ መሳሪያዎችን እጅንና ሌሎች የቆዳ ክፍሎችን ለማጽዳት መጠቀም እንደማይገባና ይልቁንም የቆዳ መቃጠልን ሊያስከትል እንደሚችል ይመክራል።

የሙቀት መለያና መለኪያ መሳሪያው "ቴርማል ስካነር" ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ሊያረጋገጥ ይችላል የሚል መላምትም ይነሳል።

ቴርማል ስካነሮች (የሙቀት መለያና መለኪያ መሳሪያ) አንድ ሰው ከመደበኛው ያለፈ የሰውነት ሙቀት እንዳለው የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል።

ነገር ግን የሙቀት መለኪያ መሳሪያው አንድ ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እንዲያውቅ እንደማያደረግና ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት የሌላቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንም ማረጋገጥ እንደማይችል አስታውቋል።

ለዚህም ምክንያቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መታመማቸውና ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት እንዳላቸው ለማወቅ ከ2 እስከ 10 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።

ሌላኛው መላምት ሁሉንም የሰውነት አካል ክሎሪንና አልኮል መርጨት ኮሮናቫይረስን ይገድላል የሚለው ነው።

ቫይረሱ ሰውነታችን ውስጥ ቀድሞ ከገባ የሰውነት አካል ክሎሪንና አልኮል መርጨት ቫይረሱን እንደማይገድልም የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

በሰውነት አካል ላይ ክሎሪንና አልኮል መርጨት ለአይን፣ ለአፍ፣ ለጆሮና ሌሎች በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስና ልብሶች ላይም ጉዳት እንደሚያደርሱ ገልጿል።

አልኮልና ክሎሪን መሬትን ለማጽዳት ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉና ለእሱም ተገቢው የባለሙያ ምክረ ሀሳቦች እንደሚያስፈልጉም ተመልክቷል።

ለሳምባ ምች (ኒሞኒያ) የሚወሰዱ ክትባቶች ሰው በኮሮናቫይረስ እንዳይያዝ ይከላከላል የሚል መላትምትም ተቀምጧል።

"ኒሞኮካል" እና "ሀሞፒለስ ኢንፍሉዌንዜ" ጨምሮ ሌሎች ለሳምባ ምች (ኒሞኒያ) የሚወሰዱ ክትባቶች አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ እንዳይያዝ አያደርገውም ይላል የዓለም የጤና ድርጅት ምላሽ።

የኮሮናቫይረስ አዲስ በመሆኑ የራሱ ክትባት እንደሚያስፈልገውና ተመራማሪዎች ለቫይረሱ ክትባት ለመፈለግ መከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

"ኒሞኮካል" እና "ሀሞፒለስ ኢንፍሉዌንዜ" ጨምሮ ሌሎች ለሳምባ ምች (ኒሞኒያ) የሚወሰዱ ክትባቶች ለመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እንዲወስዱት ይመከራልም ነው ያለው።

በጨዋማ ውሃ ወይንም ውሃን ከጨው ጋር በመቀላቀል አፍንጫን በየጊዜው መታጠብም በኮሮናቫይረስ አያድንም ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚጠቀሱ መላ ምቶች በዓለም ጤና ድርጅት ተረጋግጦ መግለጫ እስካልተሰጠባቸው ድረስ ማንም ሰው ሊተገብራቸው እንደማይገባም የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል።

በተወሰነ መረጃ የተደገፈ ቢሆንም በጨዋማ ውሃ ወይንም ውሃን ከጨው ጋር በመቀላቀል አፍንጫን በየጊዜው መታጠብ ጉንፋን የያዘው ሰው በፍጥነት ሊያገግም ይችል ይሆናል።

ነገር ግን በጨዋማ ነገሮች አፍንጫን በየጊዜው መታጠብ ሰው በመተንፈሻ አካል በሽታዎች እንዳይያዝ አይከላከልም ይላል የድርጅቱ መረጃ።

ነጭ ሽንኩርት መብላት የኮሮናቫይረስን ይከላከላል የሚል ሀሳብም ብዙ ጊዜ ይነሳል።

ሆኖም ነጭ ሽንኩርት ጤናማ ምግብና ረቂቅ ተዋህሲያንን መግደል የሚያስችሉ ባህሪዎች እንዳሉት ቢታወቅም ከኮሮና መያዝ አያስጥልም ተብሏል።

ሌላኛው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሳው ጉዳይ ኮሮናቫይረስ የሚያጠቃው በእድሜ የገፉ ሰዎችን ብቻ ነው የሚለውም አባባል ትክክL አይደለም።

ቫይረሱ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚይዝና አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመምና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው በእድሜ የገፉ ሰዎችም ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ተብሏል።

በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ኮቪደ-19 ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስቧል።

ሌላኛው መላምት የጸረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች የኮሮናቫይረስ ለመከላከልና ለማከም ውጤታማ ናቸው የሚል ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት የጸረ-ባክቴሪያ መድሐኒቶች የሚሰሩት ለቫይረሶች ሳይሆን ለባክቴሪያ ብቻ እንደሆነ ገልጿል።

የተለያዩ መድሐኒቶች የኮሮናቫይረስ ይከላከላሉ ያክማሉ የሚል መላምት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሆኖም እስካሁን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚከላከልና የሚያክም ምንም አይነት መድሐኒት ወይም የተረጋገጠ ክትባት እንደሌለ የዓለም የጤና ድርጅት አስረግጧል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አስፈላጊው ህክምና እና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸውንና በጽኑ ህመም ላይ የሚገኙ የቫይረሱ ተጋላጮች ተገቢው ክትትል ሊያገኙና አስፈላጊው ክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይመክራል።

አንዳንድ ህክምናዎች በምርምራ ላይ እንደሚገኙና በክሊኒካል ፍተሻዎች ሙከራ እንደሚደረግባቸው   የዓለም የጤና ድርጅት ያስታወቀው።

ድርጅቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ኮቪድ-19 አስመልክቶ የሚደረጉ ጥናቶችና የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ ድጋፍ እያደረገም መሆኑ ተመልክቷል።

የአሜሪካው የጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው፤ እስካሁን በዓለም በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ165 ሺህ በላይ አሻቅቧል።

ከ2 ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ ሰዎችም በቫይረሱ ሲያዙ ከ632 ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል።

በኢትዮጵያ አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አሁናዊ አሃዝ 111 የደረሰ ሲሆን ሶስት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 16 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም