ቀጥታ፡

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ከክለቦች አመራሮች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለቦች አመራሮች ጋር በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ውይይት አካሄደ። ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም በተደረገ የ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር በደጋፊዎች መፈጸሙ ይታወሳል። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ የታየው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚያመራ በመሆኑ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስተባባሪነት የቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባጅፋር አመራሮች ትናንት በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ የሁለቱ ክለቦች አመራሮች የተፈጠረውን ችግር በማውገዝ ክለቦቹ ቀደም ሲል በነበራቸው የእግር ኳስ ተሳትፎ ሰላማዊ የአብሮነት ትስስር የነበረው መሆኑን አንስተዋል። የስፖርት ቤተሰቡ ስፖርቱ በሚጠይቀው ስነ-ምግባር የታነፀ እንዲሆን የአመራሮቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ሰፊ ውይይት በማድረግና ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አቅጣጫ በማስቀመጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ በጋራ እንደሚሰራና የውድድር ዘመኑ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ መጠናቀቅ እንዲችል የሁሉም ባለድርሻ አካል ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ገልጸዋል። የክለቦቹ አመራሮች የስፖርታዊ ጨዋነትን ችግር ለመፍታት የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ሰላማዊ እግር ኳስ የሚካሄድበትን መድረክ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል። የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረ መስቀልና ሌሎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እንዲሁም የጅማ ከተማ ከንቲባና የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ መክዩ መሐመድ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። የስነ ምግባር ኮሚቴ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ፤ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ሜዳ አንድ ጨዋታ እንዲያካሂድ መወሰኑ ይታወሳል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፌዴሬሽኑ በሚያቀርበው የህክምና ማስረጃ መሰረት በክለቡ ደጋፊዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ጅማ አባጅፋር ካሳ እንዲከፍል ኮሚቴው ወስኗል። የስነ-ምግባር ኮሚቴው ፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ለጅማ አባጅፋር የቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ “የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሜዳ ገብተው ዳኛውን ለመደብደብ ሙከራ አድርገዋል” በሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይም የ50 ሺህ ብር ቅጣት አስተላልፏል። በጨዋታው ወቅት ስድስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች አምስት ቢጫና አንድ ቀይ ካርድ በመመልከታቸው የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቡድኑ አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወሳል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም