ቀጥታ፡

በባሌ ጎባ የኬሚካል ርጭት ተካሔደ

ጎባ(ኢዜአ) ሚያዚያ 11 /2012 ዓም በባሌ ጎባ ከተማ የኮሮና ቨይረስን ለመከላከል በዋና ዋና መንገዶችና በተሸከርካሪዎች ላይ የፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት መካሔዱን የከተማዋ ከንቲባ ገለፁ ።
የከተማዋ ከንቲባና የቫይረሱ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ  አቶ ንጋቱ ሞቱማ እንደገለጹት በከተማዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን እንዳይከሰትና  ከተከሰተም ፈጥኖ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ።

በትናንትናው እለትም ህዝብ በሚበዛባቸው የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች፣በሶስት እግር ባጃጆችና በተሸከርካሪዎች ላይ የፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት ተካሔዷል ።

ለመጀመሪያ ዙር በተካሄደው ርጭት 15 ሺህ ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን የገለጹት አቶ ንጋቱ በቀጣይ በየሰፈሩና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ 

የከተማዋ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ኢሳ መሐመድ በበኩላቸው የተሳፋሪዎችን የበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ በመናኽሪያ መግቢያና መውጫ አካባቢ በተሸከርካሪዎች ላይ የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት መካሔዱን ገልፀዋል ።

በኬሚካል ርጭት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል አባል አቶ ሰይፉ መሐመድ በበኩላቸው በዞኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የመከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚተላለፉ የመከላከያና የጥንቃቄ መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ አቶ ሙክታር በከር በሰጡት አስተያየት በከተማዋ ከበሽታው መከላከል ጋር ተያያዞ የሚከናወነው ተግባር መልካም ቢሆንም የመዘናጋት አዝማሚያ ስላለ  በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም