የትንሳኤ በዓል ሲከብር ሌሎችን በማሰብና በመርዳት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳኤ በዓል ሲከብር ሌሎችን በማሰብና በመርዳት ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2012(ኢዜአ) ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ስቃይ ለሁሉም በመሆኑ ነገ የሚከበረው የትንሳኤ በዓል ደጋፊ የሚያሻቸውን በማሰብና በመርዳት ሊከበር እንደሚገባ የቤተክርስቲያን መምህራን ተናገሩ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ስቃይ ለሌሎች በመሆኑ ምዕመኑም በዓሉን ሲያከብሩ ሌሎች በመርዳት ሊሆን ይገባል ይላሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወንጌል መምህር የሆኑት ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ካስተማረው አንደኛው ለራስ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን ነው። በመሆኑም በዓሉ ሲከብር እርስ በእርስ መረዳዳትና በመተሳሰብ ማሳለፍ ይገባል ነው ያሉት።
''የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤን በዓል ሲከበር ከመጠጥና ከስካር ነገሮች በመራቅ እንጂ ወደ ሞት በመሄድ ሊሆን አይገባም።''
ዲያቆን ሄኖክ የመጀመሪያው ትንሳኤ በዓል ሐዋርያት በፍርሀት በቤት ሆነው ያሳለፉበት ወቅት እንደነበር በማስታወስ፤ በዚህ ዓመት የሚከበረው ትንሳኤ በዓልም በወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ችግር ምክንያት የመጀመሪያውን ዓመት ትንስኤ አይነት ሆኗል ሲሉ ነው የተናገሩት።
የትንሳኤን በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዓመት ከምታከብራቸው 18 ዋና እና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነም ነው ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ የተናገሩት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ ለ50 ቀናት የሚከበር ነው ብለዋል።
ይህም የሚሆነው ዘላለማዊ የሆነው የመንግስተ ሰማያት ኑሮን ለማሳየት ነው ሲሉ መምህር ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ ለኢዜአ ተናገረዋል።