የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ የግእዝ ቋንቋ ስልጠና ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ የግእዝ ቋንቋ ስልጠና ሊጀምር ነው
ጎንደር ሰኔ 26/2010 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብር የግዕዝ ቋንቋ ስልጠና ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው "የኢትዮጵያ ትምህርት በአገር እድገት ያለው አስተዋጽኦ፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች’’ በሚል መሪ ቃል ሁለተኛውን አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ እያካሄደ ነው። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከ2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የግእዝ ቋንቋ ትምህርት በማታው የትምህርት መርሀግብር ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ነው። የትምህርት መርሀ ግብሩን ለመጀመር የሚያስችሉ የስርአተ ትምህርት ቀረጻን ጨምሮ የመምህራን ምልመላና ስልጠና እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል ። ትምህርቱን መስጠት ያስፈለገው በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ ድርሳናትን ወደ አማርኛ ቋንቋ በመተርጎም ለጥናትና ምርምር ስራዎች የሚውሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የግዕዝ ቋንቋ በአሁኑ ወቅት ከሃይማኖት ተቋማት ውጪ እምብዛም ለንግግርም ሆነ ለጽሁፍ ቋንቋነት እየዋለ ባለመሆኑ ህልውናውን ከማስቀጠል አኳያ የመርሀ ግብሩ መጀመር የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል። የማታ ትምህርት መርሀ ግብር ውጤታማነት ታይቶ በመደበኛው ክፍለጊዜ ስልጠናው የሚሰጥ መሆኑንም ዶክተር ደሳለኝ አመላክተዋል። የዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርት ፋካሊቲ ዲን ወይዘሮ መሰረት ሀሰን ጉባኤው "በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት ለጥናትና ምርምር ተግባራት የሚውሉ ግብአቶችን ለማሰባሰብ ያለመ ነው" ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በሃይማኖት ተቋማት የተዘጋጁ ስምንት ጥናታዊ ጽሁፎች በጉባኤው ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባኤ የክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የትምህርት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።