ቀጥታ፡

የኦርቶዶክስና የካቶሊክ የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2012( ኢዜአ) የትንሳዔ በዓልን በማስመልከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በመላ አገሪቱ ለገጠርና ለከተማ፣ ከአገር ውጪ፣ የአገሪቷን ዳር ድንበር እየጠበቁ ለሚገኙና በሕመም ላይ ላሉና ለሕግ ታራሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ብጹዕነታቸው ''በእርሱ ያመኑ ሕሙማንን ያድን ዘንድ የታመመው፣ የሞተው ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃን ትንሳኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ'' ብለዋል።

የበዓሉም መሰረት ''ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛና ስለ ደህንነታችን ሲል በለበሰው ስጋ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሳ የሚለው ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።

ክርስቶስ ይህንን ሁሉ መከራ የተቀበለውም ሰዎች የተከተሉትን የተሳሳተ ምርጫ ለማረምና ቤዛ ለመሆን መሆኑን የገለጹት ብጹዕነታቸው ''በሕመሙ ሕመማችንን፣ በሞቱ ሞታችንን፣ በመቃብሩ ሙስና መቃብርን አስወግዶ፣ በትንሳኤው ትንሳኤያችንን አስወግዶልናል'' ብለዋል።

እግዚአብሔር ፍጡራኑን እንደማያጠፋ ያብራሩት ብጹዕነታቸው "አሁን የመጣውን ኮሮና የተባለውን በሽታ ለመከላል እግዚአብሔር እውቀቱን ከሰጣቸው ባለሙያዎች የሚተላለፈውን መልዕክት መተግበር እንጂ እሱ ያውቅልና የሚለው ቸልተኝነት ማሳየት እግዚአብሔርን መፈታተንና ኃጥያትም ነው" ብለዋል።

የቅድስት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ወኪል በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ምዕመናን ቤት ሆነው እንዲጸልዩ የተላለፈው ውሳኔ እንዲሁ ዝም ብሎ አለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ሲኖዶስ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው እግዚአብሔር አንድም ሰው እንኳን በጥንቃቄ ጉድለት እንዲጎዳ ስለማይፈልግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በስውር መጾምና መጸለይ ስለሚፈቀድም ጭምር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ምዕመኑም ካህናቱም እስካሉ ድረስ እግዚአብሔር ምህረቱን በላከ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአንድ ላይ ሆኖ መጸለይ፣ ማመስገንና ማስቀደስ፤ ማምለክና መቁረብ እንደሚቻል መገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል ብጹዕነታቸው።

''በመሆኑም አሁንም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈውና ወደፊትም እንደ አስፈላጊነቱ በሚያስተላልፈው ሲኖዶሳዊ ብይን መሰረት በየቤታችሁ ሆናችሁ ከልብ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ በሽታውን እንድትከላከሉ፤ ለተቸገሩ ወገኖችም ያቅማችሁን አድርጉ'' ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ''የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ከማክበር የበለጠ ቀን የለም'' ብላለች።

የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ''የዘንድሮው በዓላችን በሃዘንና በጨለማ የተከበበ ቢመስለንም በተስፋ የተሞላን ሆነን እናከብረዋለን'' ብለዋል። 

''ምክንያቱም ጌታችን የሥጋውን ድካም ሞትን ድል በማድረግ በመንፈሳዊነት እንዳሸነፈ እኛም የሥጋን ድካም በመንፈሳዊነት እንደምናሸንፍ አውቀን በዚህ ወቅት የዓለም ደዌ ሆኖ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ እርሱ በትንሣኤው እንዲሽርልንና እንዲያጠፋልን የጀመርነውን የጸሎትና የንስሐ ልመና አምላካችን ሆይ እንደቸርነትህ ብዛት ማረን፣ ይቅር በለን በማለት አጠናክረን ልንቀጥል ያስፈልጋል'' ነው ያሉት።

''ይህን ክፉ ቀን ማለፍ የምንችለው በእምነትና በፀሎት ነውና እንበርታ፤ እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር ተፈቶ አዕምሮአችን ሰላምና ደስታ እንዲያገኝ በተለያየ መንገድ ይህን በሽታ ለመከላከል ለሚሰሩና ለሚተጉ እንዲሁም በጎ ለሚያደርጉ ሁሉ እግዚአብሔር ጥበቃውንና ፀጋውን እንዲያበዛላቸው ምኞታችንና ጸሎታችን ነው'' በማለት ለምዕመኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ክርስቲያኖችም በዚህ የትንሳኤ ክብረ በዓል ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ለወንድሞቻውና ለእህቶቻው፣ ለአገራቸው አስፈላጊውን እገዛ እና እርዳታ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም