የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን ለመከላከል እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን ለመከላከል እየሰራ ነው
ሰመራ( ኢዜአ ) ሚያዚያ 9/2012፡የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።
የዩኒቨርስቲው የጥናት፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱርህማን ከድር ለኢዜአ እንደተናገሩት ተቋሙ በሽታውን ለመከላከል የለይቶ ማቆያ ማዕከል አዘጋጅቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ከጂቡቲ በቅርቡ የተመለሱ 84 ዜጎችን ተቀብለው በማስተናገድ እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት ጠቅሰዋል።
ስለበሽታው ጉዳትና መከላከያ መንገዶችን ከክልሉ ጤና ቢሮና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪም የውሃና ሳሙና አቅርቦት ችግር ላለባቸው አርብቶ አደሮች የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር አምርቶ ለማዳረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
ዶክተር አብዱርህማን እንዳሉት በቀን 120 ሊትር ሳኒታይዘር በማምረት ላይ ይገኛሉ፤እስካሁን ያመረቱት ከ400 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ለአርብቶ አደሩ ለማከፋፈል አዘጋጅተዋል።
በዩኒቨርሲቲው መምህራን የተሰራና ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ አግባብ የሚያገለግሉ 20 የእጅ መታጠቢያም የህዝብ እንቅስቃሴዎች በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለመትከል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ በበኩላቸው የኮሮና በሽታን ለመከላከል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያሳተፉ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከባለድርሻ አካላት ውስጥም የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና የተሻሻሉ አሰራሮችን በማመቻቸት በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።