በአዳማ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 55 አሽከርካሪዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 55 አሽከርካሪዎች ተቀጡ
አዳማ፤ ሚያዝያ 09/ 2012 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያ ተላልፈው የተገኙ 55 አሽከርካሪዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን በአስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አሰታወቀ።
የግብረ ኃይሉ አባል ኮማንደር አለማየሁ በቀለ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት አሽከርካሪዎቹ የተቀጡት መመሪያውን ተላልፈው ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ትርፍ በመጫንና ከተፈደላቸው ውጭ አገልግሎት ሲሰጡ በመገኘታቸው ነው።
በዚህም እያንዳንዳቸው 2ሺህ እስከ 5ሺህ ብር መቀጣታቸውን አመልክተዋል፡፡ ቅጣቱ ከተላለፈባቸው መካከልም የባጃጅ፣ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የህዝብ ማመላለሻ ዶልፊን፣ የቤት አውቶሞቢልና ከባድ የጭነት አሽከርካሪዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ግብረ ኃይሉ ቫይረሱን ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ በተጓዳኝ አዋጁን በማስፈፀም ረገድ መመሪያውን በሚተላለፉ ማንኛውም አካላት ላይ የሚወሰድ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር አለማየሁ ገልጸዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የግብረኃይሉ ሰብሳቢ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው በተለይ አዋጁን ለማስፈጸም የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሁሉም የፀጥታ አካላት በትብብር እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በከተማዋ ውስጥ ባጃጅ አንድ ሰው እና የሚኒባስ ታክስ ደግሞ ስድስት ሰዎች ብቻ በመጫን ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ከአዳማ ከተማ ወደ ዞኖችና ወረዳዎች በሚደረገው ጉዞ ላይ ያጋጠመውን የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት እጥረት ለማቃለል ከትራንስፖርት ማህበራትና ባለንብረቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑም አስረድተዋል።