ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ

ባህርዳር ሚያዚያ 9/2012 የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። 
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ ለኢዜአ እንደገለጹት የትንሳኤ በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ከክልል እስከ ቀበሌ የሚገኘው የፀጥታ ኃይል በዓሉ በሰላም እንዲከበርና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎች እንዲተገበሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓመታዊ በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበርም በየደረጃው ያሉ ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር እንዲሰሩ የሚያስችል አደረጃጀቱ ተፈጥሯል።

ለበዓሉ በሚደረግ የገበያ እንቅስቃሴ ስርቆት ፣ ዝርፊያና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳይፈጠር ማህበረሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኮማንደሩ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የዚህ ዓመት የትንሳኤ በዓል ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆኖ የሚከበር በመሆኑ ሰፊ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል ።

በማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ማህበረሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች ማክበርና ማስከበር እንደሚገባም ኮማንደር መሰረት አሳስበዋል ።

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ጥርጣሬዎችንና የወንጀል ምልክቶችን ሲያይም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ አካላት  ጥቆማ በመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም