የስቅለት መርሃ ግብር በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለምዕመኑ እየደረሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስቅለት መርሃ ግብር በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለምዕመኑ እየደረሰ ነው
አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች ስርዓት ሕማማቱንና ስግደቱን በቤተቸው ሆነው እየተከታተሉና እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን አበይት በዓላት ከምታከብራቸው መካከል ስቅለት አንዱ ነው።
እለቱ ምዕመናን ለሁለት ወራት በጾምና ጸሎት ካሳለፉ በኋላ በዚህ ዕለት በቤተ ክርስትያን ቅጥር ጊቢ ውስጥ በአንድነት ተሰብስበው እየሱስ ክርስቶስ ለስው ልጆች ሁሉ ሲል የከፈለውን መስዋዓትነት የሚያስቡበት ዕለትም ነው።
''የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ'' ተብሏል።
ኮቪድ 19 ወረርሺኝ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ መንግስት በዋጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በዘንድሮው ስቅለት ምዕመኑ በአንድነት ሆኖ ኃይማኖታዊ ክዋኔውን ማድረግ አይችልም።
የቤተ ክርስቲያኗ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ዕለቱን አስመልክተው ለኢዜአ እንደተናገሩት መዕመኑም በቤቱ ሆኖ ኃይማኖታዊ ስርዓቱን እያከናወነ ሲሆን አድባራትና ገዳማቱም የተለመደውን ስርዓት እያከናወኑ ይገኛሉ።
ቤተክረስትያኗ የወቅቱን ሁኔታ ባማገናዘበ መልኩ በዕለቱ የሚደረገውን ሙሉ ስርዓት በመገናኛ ብዙሃን ለምዕመኑ ቀጥታ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ብለዋል። ለዚህም መገናኛ ብዙሃንን አመስግነዋል።
አሁን ያጋጠመው ወቅታዊ ዓለም ዓቀፋዊ ችግር እንደመሆኑ መጠን ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል የባለሙያዎች ምክር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አስታውሳዋል።
በዚሁ መሰረት ''ምዕመኑ ይችን ታለቅ ዕለት በቤቱ ሆኖ እንዲጸልይና እንዲሰግድ ተደርጓል'' ብለዋል ዶክተር አቡነ አረጋዊ።
ወቅቱ ድንገተኛና አዲስ ነገር ይዞ ቢመጣም ሙሉ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን ምዕመናን በርከት ብለው በቤተክርስትያን ግቢ ውስጥ ካለመገኘታቸው በስተቀር የተጓደለ ነገር የለምም ነው ያሉት።
በመሆኑም ምዕመኑ የወቅቱን ከባድነት በመረዳት በስቅለትም በትንሳኤም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትን ሳይረሳ፣ መካፈልን መርሳት የለበትም ሲሉ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
''በዚህ ጊዜ ሰዎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ አንዳንድ ወገኖች መቸገራቸው ስለማይቀር እነርሱንም በመርዳት ማሳለፍ ያስፈልጋል'' ብለዋል።
እርድ ሲፈጸምም ሕዝቡ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ከጤና ባለሙያዎች በአግባቡ መረዳት እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር አቡነ አረጋዊ ''የዱሮ ዓይነት የደስታ አገላለጽ ላይኖር ይችላል፣ በየቤቱ ቤት ያፈራውን በጥንቃቄ፣ በማስተዋል መሳተፍ ያስፈልጋል'' ነው ያሉት።
ምዕመናን በስክል እየተጠያየቁ አስተዋሽና ጠያቂ የሌላቸውን አካላዊ ርቀትን ጠብቀው ኃይማኖት የሚፈቅደውን ተግባር መከወን ግዴታ መሆኑንም እንዲሁ አሳስበዋል።
''ኢትዮጵያውያን የሚደነቅ መንፈሳዊና ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ያለቸው ሕዝቦች ናቸው'' ያሉት ዶክተር አቡነ አረጋዊ ይህን ቸነፈር ለማለፍ በመሸበር ሳይሆን በዕምነቱ ጸንቶ፣ ጥንካሬውን ለጥንቃቄ በማዋል ችግሩን ሊያልፍ ይገባል'' ብለዋል።
''ሁሉም ባለበት ሆኖ በእምነቱ ጸንቶ "እንድናለን" ብሎ ለእግዚያብሔር ያለውን ታማኝነት በመግለጽ ጊዜውን ሊያልፍ ይገባል'' ሲሉ ለምዕመኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።