የግል ወይም የቤት መኪና አሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ ተወሰነ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የግል ወይም የቤት መኪና አሽከርካሪዎች የሰሌዳ የመጨረሻ ቁጥራቸው ሙሉ አና ጎደሎ በሚል በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ የሚያስገድድ መመሪያ ይፋ ሆነ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የወጣውን ደንብ ተከትሎ የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም መመሪያ ዛሬ ይፋ ሆኗል።


የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ መሆኑ ይተወቃል።

አዋጁን ለማስፈፀም የወጣውን ደንብ ተከትሎም በዛሬው እለት የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም መመሪያ ይፋ ሆኗል።

መመሪያው አጠቃላይ 5 ክፍሎች ያሉት እና በ23 አንቀጽ የተዋቀረ ሲሆን አባሪ 2 መመሪያዎችን የያዘም ነው።

በክፍል አንድ አጠቃላይ ድንጋጌዎች፣ በክፍል ሁለት የትራንስፖርት፣ የመናሀሪያ፣ የደረቅ ወደብ እና ሎጀስቲክ አጠቃቀምን የተመለከተ ሲሆን ክፍል ሶስት ደግሞ የሰራተኞች መግቢያና መውጫ ሰዓትን ተመልክቷል።

ከፍል አራት ግብረ ሃይል ስለመቋቋም ሲደነግግ ክፍል አምስት ደግሞ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በማስቀመጥ ሁለቱ አባሪ መመሪያዎች ደግሞ የጭነት ልክ እና የስምሪት መስመሮች ላይ የተደረጉ የመውጫ ሰዓት ማሻሻያዎች ናቸው።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ የወጣውን መመሪያ በተመለከተ መግለጫ ሰተዋል።

በመግለጫቸውም በመመሪያው የግል ወይም የቤት  ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ ተወስኗል ብለዋል።

የግል ወይም የቤት መኪና አጠቃቀምን በተመለከተ፤ መጠቀም የሚቻለው የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ጎዶሎ ቁጥር በሚል በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ ሆኗል።

የመጨረሻ ሰሌዳ ቁጥራቸው ሙሉ የሆነ የግል ተሽከርካሪዎች ይህ መመሪያ ከፀደቀበት ቀን ቀጥሎ ባለው ቀን መንቀሳቀስ የሚችሉ ሲሆን የሰሌዳ የመጨረሻ ቁጥራቸው ጎደሎ የሆኑት በዚህ እለት መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸውም።

በመሆኑም የመጨረሻ ቁጥራቸው ጎደሎ የሆነ የግል ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ የሚፈቀድላቸው በሚቀጥለው ቀን ይሆናል።

የሰሌዳ ቁጥራቸው መጨረሻው ዜሮ የሆኑ ተሽከርካሪዎች እንደ ሙሉ ቁጥር ተደርጎ የሚታይ መሆኑም ተገልጿል።

ከስራቸው ፀባይ አንፃር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በደንቡ ወይም በመመሪያው የሚሳተፉ ሰዎች ከባለስልጣኑ በሚሰጣቸው ልዩ የይለፍ ፈቃድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል።

መመሪያው በመላ አገሪቱ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን የአገር አቋራጭ፣ የከተማ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከመደበኛው ወንበር ልካቸው  50 በመቶ ብቻ መሆኑን መመሪያው አስቀምጧል።

ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ደግሞ መጫን የሚችሉት ከአሽከርካሪውን በተጨማሪ አንድ ሰው ብቻ ነው።

የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪዎች በህግ ከተፈቀደላቸው የመጫን አቅም 50 በመቶ ብቻ መሆኑንም እንዲሁ አስቀምጧል።

የጭነት ተሽከርካሪዎች ደግሞ መጫን የሚፈቀድላቸው ከአሽከርካሪው በተጨማሪ አንድ ሰው ብቻ መሆኑንም መመሪያው አስቀምጧል።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ደንቡ አፈፃፀም ለአገርና ለህዝብ ደህንነት አገልግሎት የሚሰጡትን የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ፣ አምቡላንስ፣ የእሳት አደጋ እና የመንግስት መኪኖች የዚህ መመሪያ ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንባቸውም።

ለትራንስፖርት አገልግሎት የተፈቀደ ሰዓትና የታሪፍ ጭማሪን በተመለከተ ማንኛውም የአገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚችለው ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ብቻ መሆኑንም ያመላክታል።

በዚህ መመሪያ መሰረት አገልግሎቱን ሲሰጡ የታሪፍ ጭማሪ በተመለከተ ከመደበኛ ዋጋው 50 ከመቶ ጭማሪ እንደሚኖረው እና ዝርዝሩ በባለስልጣኑ እንደሚወሰን ተናግረዋል።

የመናሀሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ መናሀሪያዎች ማስተናገድ የሚችሉት የእለት ስምሪት ከመደበኛው ጊዜ የስምሪት መጠን 50 በመቶ ብቻ ነው።

መመሪያው በሚኒስትሮች ኮሚቴ ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ የፀና እንደሚሆን እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈፃሚነት ዘመን ውስጥ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ አስቀምጧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳም የዚህ መመሪያ ተፈፃሚነት አብሮ እንደሚነሳ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም