በአዳማ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ ነው
አዳማ (ኢዜአ) ሚያዝያ 09/2012 በአዳማ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የአስተዳደሩ የበሽታው መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በጎዳና ላይ ጭምር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በተጓዳኝም የሙቀት መጠን ልኬት ቤት ለቤት መጀመራቸውንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለሥራው ውጤታማነት በከተማው 18 ቀበሌዎችና ክፍለ ከተሞች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የለይቶ ማቆያና ህክምና መስጪያ መዘጋጀቱን ያመለከቱት ከንቲባው በከተማዋ እስካሁን ባለው ሂደት ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዝብና በዓይነት ከባለሃብቶች በድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።
"በከተማዋ የበሽታው ምልክት የሚያሳዩት ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ በመውሰድ ክትትል እያደረግን ነው" ያሉት ደግሞ የግብረ ኃይሉ ፀሐፊና የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ሰሚራ ሙሐመድ ናቸው።
በመንግስትና የግል ጤና ተቋማት የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በትብብር የቤት ለቤት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ ከመንግስት ፣ጤና ባለሙያዎች፣ ሀዳ ሲንቄዎች፣ አባገዳዎችና የኃይማኖት መሪዎች የሚተላለፈውን መልዕክት በመተግበር በሽታውን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበትም ሲስተር ሰሚራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዳማ ከተማ አስተዳደርና ምስራቅ ሸዋ ዞን የቀይ መስቀል ቅርንጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቡሰሪ ቡና በበኩላቸው "የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከጤና ባለሙያዎች ጋር ሆነን ግንዛቤ በማስጨበጥ ዙሪያ በቅንጅት እሰራን ነው " ብለዋል።
ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲያግዙ ጽሕፈት ቤቱ ያሉትን አምቡላንሶች ማሰማራታቸውንም ተናግረዋል።
ሠራተኞቻቸው እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ከከተማዋ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።