የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማሕበር ለኮቪድ- 19 መከላከያ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማሕበር ለኮቪድ- 19 መከላከያ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማሕበር ለኮቪድ- 19 መከላከያ እንዲሆን የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የማሕበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ኦላኒ ሴቃታ፤ የባንኩ ሰራተኞች በዚህ ወሳኝ ጊዜ ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑን በመግለጽ በተለያዩ ጊዜ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ይናገራሉ።
ማሕበሩ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተደጋጋሚ ጊዜ ቦንድ ከመግዛት በተጨማሪ ለቀይ መስቀልና መቄዲኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህ ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በአገር ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የሰራተኞቹን ጤንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
የኮቪድ-19 ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላትም ማሕበሩ ያደረገው ተግባር ለሌሎች መሰል ተቋማት ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግና የኮሚቴው አባል ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ማሕብሩ ለትርፍ ያልተቋቋመ እንደመሆኑ ያደረገው ድጋፍ ትርፋማ ለሆኑ ድርጅቶች ትልቅ መልዕክት አለው ብለዋል።
የቫይረሱ አጠቃላይ ሁኔታ ድንገተኛና አዲስ በመሆኑ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በጋራ መቆም ግድ ይላልም ነው ያሉት።
በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የቀን ገቢን ተማምኖ የሚኖር በመሆኑ እንቅስቃሴ ሲገታ ብዙ ሰው ለችግር ስለሚዳረግ፤ መንግስት እነዚህን ለችግር የሚጋለጡ ቤተሰቦችንና አቅም የሌላቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመርዳት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ነው የገለጹት።
ገቢ ስላለ፤ ገንዘብ ስላለ ከበሽታው ማምለጥ ስለማይቻል ሁሉም ሰው ራሱን ከመጠበቅ ጎን ለጎን መተጋገዝ ይኖርበታል ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።
ማሕበሩ ያደረገው ድጋፍ ትልቅ ትርጉምና ያለው ነው ያሉት የኮሚቴው አባልና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብረሃም በለይ ናቸው።
ሰራተኞቹ ካደረጉት ድጋፍ ጎን ለጎን የባንክ ስርዓቱ ሳይስተጓጎል፤ አገልግሎቱም እንዲሳለጥ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጾም ያስመሰግናቸዋል ነው ያሉት።
ሌሎችም ከዚህ ተግባር በመማር በመተጋገዝ ይሄን ወቅት በጋራ ማለፍ ያስፈጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለዚሁ ተግባር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች 54 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ባንኩ ከ60 ሺህ በላይ ሰራተኞች ሲኖሩት 24 ሚሊዮን ደንበኞችንም አፍርቷል።