ቻይና በኢትዮጵያ ያለውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የባለሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና በኢትዮጵያ ያለውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የባለሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች
ሚያዚያ 8 / 2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተደረገ ባለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የመከላከል ስራ ላይ የሚሰማራ 12 አባላትን የያዘ የህክምና ቡድንና በርካታ ቁሳቁሶች በዛሬው ዕለት ከቻይና አዲስ አበባ ገብቷል።
ቡድኑ የጸረ-ወረርሽኝ ህክምና ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን ''በተባበረ ክንድ እናሸንፋለን'' በሚል መሪ ሃሳብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ከቻይና የመጣ ነው።
የሕክምና ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስተ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።
ባለሙያዎቹ ለሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ የሚቆዩ ሲሆን ቫይረሱን ከመከላከልና ህክምና ከመስጠት ለኢትዮጵያዊያን መልካም ተሞክሮን ያካፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ የህክምና ቡድኑ የኮቪድ-19 ስርጭት ለመላከል የየያስችሉ ዋና ዋና ስራዎችን በተመለከተ ድጋፍ ያደርጋል።
በተለይም ከላብራቶሪ ምርመራ፣ ከጽኑ ህሙማን ህክምና እና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎች ጋር በተያያዘ ያሉ የቻይናን ተሞክሮ የቡድኑ አባላት እንደሚያካፍሉ ተናግረዋል።
የመከላከል ጥረቱን ውጤታማ ለማድረግም በቻይና ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ በማሄድ ልምድ የሚቀሰም መሆኑን ገልጸዋል።
ከህክምና ቡድኑ ጋር ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ እንደ ጓንት፣ የአፍ መሸፈኛና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችም ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል።
ለተደረገው የባለሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ''ድጋፉ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ጥረት የበለጠ የሚያጠናክር ነው'' ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በበኩላቸው ድጋፉ ሁለቱ አገሮች ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት የሚያሳይና ኢትዮጵያ ያላትን የመከላከል አቅም እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ በቻይና የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ረገድ ቀዳሚ ሚና ያላቸው መሆናቸውንና ለኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጥሩ ልምድ ሊያካፍሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል።