ቀጥታ፡

ንግድ ባንክ የሆቴልና መሰል አገልግሎት ደንበኞቹ ያቀረቡለትን የብድር እፎይታ ጥያቄ ለመመለስ ጥናት እያደረገ ነው

ሚያዚያ 8 / 2012  (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆቴልና መሰል አገልግሎት ዘርፍ ደንበኞቹ ያቀረቡለትን 'የብድር እፎይታ ጊዜ ይሰጠን' ጥያቄ ለመመለስ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ለተሰማሩት ደንበኞቹ ደግሞ የወረርሽኙ የወደፊት ሁኔታ ታይቶ የሚወሰን ይሆናል ።

የዓለምን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በመግታት ሁለንተናዊ ቀውስ እያስከተለ ያለው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ደካማ ኢኮኖሚ ላይ 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' መሆኑ አልቀረም።

ይህን ተከትሎም በተለያዩ ኢኮኖሚ መስኮች የተሰማሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ድርጅቶች የብድር ክፍያ ጉዳይ ከወዲሁ እንዳሳሰባቸው ሲገልጹ ይስተዋላል።

በሆቴልና መሰል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞች የወቅቱን ዓለም አቀፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከትሎ ተቋማቱ ባጋጠማቸው የገበያ ሁኔታ ከባንክ የወሰዱት ብድር የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ለአበዳሪ ባንኮች ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ለጋራ መኖሪያ ቤት ደንበኞቹ የብድር እፎይታን ማድረጉን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች የተሰማሩ ድርጅቶች ለባንኩ የብድር መክፈያ ጊዜ ይራዘም የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አምነው፤ አብዛኞቹ ደንበኞች ግን አስቀድመው ችግሩን በመፍራት ይከሰታል በሚል ስጋት እንጂ በተግባር ችግሩ ደርሶባቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በሽታው ተገማች ባለመሆኑና የሚያደርሰው የጉዳት መጠን ባለመታወቁ ባንኩ ለደንበኞቹ ይህን አደርጋለሁ በሚል በአጭር ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ አለመኖሩን ገልጸው "ወደፊት በጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል" ብለዋል።

የሰዎች እንቅስቃሴ በመገታቱ ሆቴሎች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ኪሳራ ሊደርስ እንደሚችል ያመኑት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህም የሆቴል ማህበራት ሳይቀር በጉዳዩ ላይ ለባንኩ ማመልከቻ ማስገባታቸውን አረጋግጠዋል።

"ደንበኞች የሚደርስባቸውን ችግር በሙሉ ባንሸከምም የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመጋራት ዝግጁ ነን" ብለዋል።በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶች የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ከማራዘም ባሻገር ሊደረግላቸው የሚገባውን ድጋፍ ለመለየት ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም