ቀጥታ፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ እናኑ አሰምሬ የግል ሕንጻቸውን ለኮሮና መከላከል ተግባር እንዲውል ሰጡ

ሚያዚያ 8 / 2012  (ኢዜአ)  በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ እናኑ አሰምሬ በወር እስከ 200 ሺህ ብር የሚከራይ የግል ሕንጻቸውን ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መከላከል ተግባር እንዲውል ሰጡ። 

ለተለያዩ የቢሮ አገልግሎቶች ተከራይቶ እስከ 200 ሺህ ብር ወርሃዊ ገቢ የነበረውን ሕንጻ በዛሬው እለት ባለቤቷ ወይዘሮ እናኑ ለጤና ሚኒስቴር አስረክበዋል።

ሕንፃውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃርላ አብዱላሂ በቦታው ተገኝተው የተረከቡ ሲሆን ከ50 እስከ 60 አልጋዎችን ይይዛል ተብሏል።

በኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ላይ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ጊዜያዊ መኖሪያ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተገልጿል።

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ የተናገሩት ወይዘሮ እናኑ፤ የመንግስትን ጥረት ለመደገፍ ህንጻውን በጊዜያዊነት መስጠታቸውን ገልጸዋል።

"ቫይረሱን ለመከላከል እየታገሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ራሳችንን ከቫይረሱ በመጠበቅና ያለንን በመለገስ ልንረዳቸው ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃርላ አብዱላሂ ግለሰቧን ለበጎ ተግባራቸው አመስግነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሞራል ድጋፍ ጀምሮ በሚችለው ሁሉ ከጤና ባለሙያዎች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ወይዘሮ እናኑ አሰምሬ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው ለ37 ዓመታት ያገለገሉ ኢትዮጵያዊት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም