ቀጥታ፡

አምራቾች ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ሳኒታይዘር ለማምረት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2012(ኢዜአ) ይእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር)ን ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ ተቋማት ለግብዓት ጥራት ትኩረት እንዲሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አሳሰበ።

በባለስልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ምሬሳ ሚደቅሳ ለኢዜአ እንዳመለከቱት አምራቾቹ በተለይ የኮሮና ቫይረስን መከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ለመሆን መሥራት አለባቸው።

አምራቾቹ የጤና ሚኒስቴር ቫይረሱን ለመከላከል ያወጣቸውን መስፈርት ያሟሉ  ጥራትና  ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲያመርቱ አስገንዝበዋል።

አምራቾቹ የማምረቻ ከባቢን ጨምሮ የሚጠቀሟቸው  ግብዓቶች ቫይረሱን  የመግደል  አቅምና የጥራት ደረጃውን   ለመወሰን እንደሚያስችል ገልጸዋል ።

ተቋሙ  ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

አምራቾቹ የምርት ክትትል፣ ቁጥጥርና ማረጋገጫቸው የጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት ቢሆንም፤ አልኮል ለብቻ ሲመረትና በሳኒታይዘር ውስጥ  ሲደባለቅ መጠኑ እንደሚለያይ ተናግረዋል።

አሮማ ሳኒቴሽንና ኮስሞቲክስ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት ዶክተር አባይነህ ጌታቸው ምርታቸውን መስፈርቱን አሟልተው ለማምረት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ሆኖም ምርቱን 80 በመቶ የአልኮል መጠንን ለማዘጋጀት ያለውን እጥረት ጨምሮ  ጥራቱን የሚወስኑ ግብዓቶች  ችግር ገጥሞናል ብለዋል።

ምርቱን ከገቢ ምንጭነት ባለፈም ኅብረተሰቡን ከቫይረሱ  ለመታደግ ግብዓቶች  ተጠቅመው ለማምረት  መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 72 ተቋማት ወደ ንጽህና  መጠበቂያ  ምርት  መግባታቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም