ቀጥታ፡

አገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 8/2012 (ኢዜአ) አገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ መጀመሩን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እንዲጀመር መደረጉን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው ለኢዜአ ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በላምበረት፣ በመርካቶ ዋናው መናኸሪያና ትንሿ መናኸሪያ፣ በአስኮ፣ ቃሊቲና አየር ጤና መናኸሪያዎች መጀመሩንም አመልክተዋል።

"ተሳፋሪዎችን የመመዝገብ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሟሟላትና አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

በሁሉም መናኸሪያዎች ሰልፍ ባለባቸው ቦታዎች ርቀትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ቀለም ከመቀባት ጀምሮ አስተባባሪዎችን በመመደብ ተሳፋሪዎች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ተሳፋሪዎች ወደ መናኸሪያ ሲገቡና ትኬት ሲቆርጡ እጃቸውን በውሃና ሳሙና እንዲታጠቡ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ይግዛው ያስረዱት።

በሁሉም መናኸሪያዎች የጥንቃቄ መልዕክቶች እየተላለፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ተሳፋሪዎች ወደሚጓዙባቸው አካባቢዎች ሲደርሱ አስፈላጊው የንጽህና መጠበቂያዎችን እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው የክልል አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

የተሳፋሪዎችን ሙቀት ለመለካት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን በሁሉም መናኸሪያዎች በማሰራጨት የሙቀት ልኬት ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የአገር አቋራጭ እንዲሁም የአነስተኛና መለስተኛ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ለትራንስፖርት ማህበራት ሠራተኞች፣ ለአሽከርካሪዎች፣ ለገንዘብ ተቀባዮችና ለረዳቶች ጓንት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እንዲቀርብ ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል።

የጫኝና አውራጅ ማህበራት እና የስነ-ስርዓት አስከባሪ አደረጃጀቶች ለጫኝና አውራጅ ጓንት እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማቅረብ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።


የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ ተሽከርካሪዎቻቸው ሥምሪት ከመውሰዳቸው በፊት ከመናኸሪያው አስተዳደር ጋር በመሆን ቫይረሱን የሚያመክን ኬሚካል ርጭት ማካሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች 50 በመቶ ብቻ ተሳፋሪ እንደሚጭኑና ተሳፋሪ እጥፍ ክፍያ እንደሚከፍልም ገልጸዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን እንዲሁም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖችን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላትን ያካተተ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም