በአዲስ አበባ የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየወሰዱት ያለው እርምጃ አበረታች ነው ...ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየወሰዱት ያለው እርምጃ አበረታች ነው ...ተገልጋዮች
አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየወሰዱት ያለው እርምጃ አበረታች መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡
ተቋማቱ ''የቫይረሱ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን ደንብ እየተገበርን ነው'' ብለዋል፡፡
ኢዜአ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮ-ቴሌኮም ተገልጋዮችንና የሥራ ሃላፊዎችን አነጋግሯል፡፡
ከተገልጋዮቹ አቶ መርዕድ አድማሱ የተባሉ ነዋሪ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ደንበኞች ርቀታቸውን ጠብቀውና እጃቸውን ታጥበው እንዲገለገሉ አድርጓል።
ባንኩ እየተከተለው ያለው የጥቃቄ እርምጃ የኮሮናቫይረስ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችም በተመሳሳይ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ በማጠናከር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በባንኩ ደንበኞች አገልግሎት የሚታየው እንቅስቃሴ በትራንስፖርትና በሌሎች የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን መተፋፈግ ለመቀነስ መዋል እንደሚገባውም አመልክተዋል።
ወጣት ትርሲት ገብርዬ በበኩሏ፤ "ባንኩ ለተገልጋዮች የንፅህና አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የግንዛቤ ፈጣራ ስራ እያደረገ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው" ብላለች፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ባንኩ ባሉት ከ1 ሺህ 500 በላይ ቅርንጫፎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ደንበኞች የባንኩን አገልግሎት ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲያገኙ መደረጉንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪ ባንኩ በዘረጋቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችና በእጅ ስልኮቻቸው በመጠቀም ንክኪ ለመቀነስ የሚያስችል አማራጭ ማቅረቡን ገልጸዋል።
የባንኩ ደንበኞችና ኅብረተሰቡ በገንዘብ ዝውውር ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ለማስቀረት ከግብይት በኋላና በፊት እጆቹን እንዲታጠብ አሳስበዋል፡፡
አቶ መስፍን ኃይለሥላሴ የተባሉ ነዋሪ ኢትዮቴሌኮም ለደንበኞቹ የሙቀት ልኬት በማድረግና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በማቅረብ እያስተናገደ እንደሆነ መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮ-ቴሌኮም የአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሱፐርቫይዘር አቶ አያሌው መንግሥቱ፤ "በአገልግሎት ሂደት የተወሰነ ክፍተት ቢኖርም ደንበኞች የሙቀት ልኬት በማድረግ እጃቸውን ታጥበውና አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ከወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ላይ በተራ ቁጥር 23 ና 24 ከተዘረዘሩት እንደ ባንክ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ-ቴሌኮምና ሌሎችም ህዝብ የሚበዛባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና አካባቢዎች ላይ ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች በሆነ ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ ብሎም በማንኛውም መልኩ ስራን አለመስራት፣ ማቋረጥ፣ ማስተጓጎልና መሰል ተግባራትን መፈጸም መከልከሉ ተደንግጓል፡፡