ቀጥታ፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኮሮናቫይረስ መከላከያና ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2012(ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መከላከያና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ  አደረገ።


ተቋሙ ዛሬ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሰባት ሚሊዮን ብር ሲለግስ፤ ለግድቡ ግንባታ ማስፈፀሚያ እንዲውል 3 ሚሊዮን ብር ሰጥቷል።

የአገልግሎቱ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ድጋፉን ለኮቪድ-19 ብሔራዊ  የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና ለግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ስላሴ አስረክበዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ተቋሙ የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ከሕዝብ ጎን በመቆም አለኝታነቱን ለማሳየት ድጋፉን ማድረጉን አስታውቀዋል።

ድጋፉን የተቋሙ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ተቀናሽ በማድረግ መለገሳቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር ምስጋናው አረጋ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አገርና ህዝብን ማዳን በሚጠይቅበት ወቅት መሆኑን ተረድቶ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ኅብረተሰቡም ቫይረሱ ከሚያስከትለው ችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ሮማን በበኩላቸው ተቋሙ ለግድቡ ግንባት ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከህዝቡና ከተቋማት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረው ''ጤናችን ይጠበቃል፤ ግድቡም ይጠናቀቃል!'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም