ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙኃን ለኮቪድ-19 ዘገባ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2012( ኢዜአ) የመገናኛ ብዙኃን በተለይ ለወቅታዊው የዓለም ጤና ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ዘገባ የቃላት አጠቃቀምም ሆነ አገላለፅ ጥንቃቄ ማድርግ እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የዓለም ወረርሽኝ ሆኖ በርካቶችን ለህመምና ለሞት እየዳረገ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

በዓለም ላይ እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ127 ሺህ በላይም ህይወታቸው አልፏል።

በ185 የዓለም አገሮች ቫይረሱ ተከስቶ ለመከላከል የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድርግ ላይ ሲሆኑ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎችም ከህመሙ አገግመዋል።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ዓለም አቀፍ ወረርሽኙን በሚዘግቡበት ወቅት ለቃላት አጠቃቀማቸውና አገላለፃቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ ሰብለ ኃይሉ እንደሚሉትም የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ ታማሚዎች እንዲገለሉ የሚያደርግ መሆን የለበትም።

በዚህ ዙሪያ ዘገባዎች ትክክለኛ መረጃን የያዙና ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንጂ የሚያስፈራሩና የሚያስበረግጉ መሆን እንደሌለባቸውም ይመክራሉ።

አሁን ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ስለ ኮሮናቫይረስ የሚሰሙ ቃላቶችና አገላለፆች ከማስተማርና መረጃ ከመስጠት ይልቅ የሚያስበረግጉ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

በዘገባ ወቅት ሌላ ትርጉም የሚሰጡና ግልፅ ያልሆኑ ቃላትና አገላለጾችን መጠቀምም ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ እንደሚሉትም በዚህ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ድርብ ሃላፊነት አለባቸው።

ሚዲያዎቹ መረጃ ከመስጠት ባለፈ በማስተማር፣ ህዝቡን በማንቃትና በማስተባበር ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸውም መክረዋል።

የመገኛ ብዙሃኑ ለቃላት አጠቃቀማቸውና አገላለፃቸው ጥንቃቄ አድርገው ሊዘገቡ ይገባልም ነው ያሉት።

የኮሮናቫይረስን በማስመልከት የሚቀርቡ ዘገባዎች የሙያ ስነ ምግባርን የተከተሉና የጤና ባለሙያዎችን ትክክለኛ አገላለፅ የተከተሉ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የመገናኛ ብዙሃኑ የብሮድካስት ህጉን አክብርው መስራት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም