ለትንሳኤ በአል የአቅርቦት እጥረት አያጋጥምም - ኢዜአ አማርኛ
ለትንሳኤ በአል የአቅርቦት እጥረት አያጋጥምም
አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2012 (ኢዜአ) አገራዊ የገበያ ማረጋጋት ግብረ ሃይል ለትንሳኤ በዓል የአቅርቦት እጥረት እንደማያጋጥም አስታወቀ ፡፡
በበዓሉም ይሁን በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ሰበብ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ዜጎች የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ግብረ ሃይሉ ጥሪ አቅርቧል።
ግብረሃይሉ ያለፈው ሳምንት እንቅስቃሴውን በማስመልከት ውይይት ያካሄደ ሲሆን የገበያ ማረጋጋት ስራው የምርት አቅርቦት መኖሩን ብቻ ሳይሆን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው መድረሱን ማረጋገጥ ተችሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታና የግብረሃይሉ ሰብሳቢ አቶ እሸቴ አስፋው እንደገለጹት፤ ግብረሃይሉ በቫይረሱ መከሰት ምክንያት ከሚሰራው የገበያ ማረጋጋት ጎን ለጎን በትንሳኤ በዓል የምርት አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በአቅርቦቱ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ የአክሲዮን ማህበራትና የግል ንግድ ድርጅቶች እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ በቂ አቅርቦት መኖሩንም አስታውቀዋል።
የተቋቋመው ግብረሃይል ቀደም ብሎ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ ምንም አይነት የምርት አቅርቦት እጥረት እንደሌለ አረጋግጠዋል።
በገበያው ላይ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ነጋዴዎችንም በጥናት በመለየት ርምጃ መውሰድ መጀመሩንና ርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመልክተዋል።
እስካሁን በነበረው ሂደትም 10 ሺህ 350 የፅሁፍና የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 11 ሺህ የተለያዩ ቅጣቶች፣ 940 የንግድ ፈቃድ የመሰረዝ፣1ሺህ 300 የንግድ ፈቃድ እገዳ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በ425 ህገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች ላይ የእስርና ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ህገወጥ ንግድን ለመከላከልም የመንግስትን ጥረት ህብረተሰቡና መገናኛ ብዙሃን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
በግብይት ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ተገቢውን አላዊ ርቀት ጠብቆና ተረጋግቶ እንዲያከናውንም አቶ እሸቱ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ መሰረት የአትክልት ተራ ገበያ ወደ ጃንሜዳ መዘዋወሩ ትክክለኛ ውሳኔ ቢሆንም አሁንም የቀሩ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
''በመሆኑም በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ህጋዊና ህገ-ወጦቹን የመለየትና የህዝብ መጨናነቁን የመቀነስ ስራ ይሰራል'' ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ በ2012 ዓ.ም ያለው የግብርና ምርት መጠን 335 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን ይህም በ2011 ዓ.ም ከተሰበሰበው 315 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር በ20 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው።
በመሆኑም የአገራዊ የገበያ ማረጋጋት ስራው በትክክል ከተሰራና ህብረተሰቡ በንቃት ከተሳተፈ ''የአቅርቦት እጥረት አይገጥመንም'' ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።