ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየደረሰበት ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ዓለም አቀፍ ወረርሺኝ ምክንያት እየደረሰበት ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ። 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን በማስመልከት እያደረገ ያለውን ቅድመ ጥንቃቄ ለመገናኛ ብዙሃን አስጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ከጉብኝቱ በኋላ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ እየደረሰበት ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው።

በዚሁ ወቅትም 90 የሚሆኑት የመንገደኛ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች ግን ስራ ፈትተው መቆማቸውን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በዚህ ወቅት ከቫይረሱ ስርጭት አንጻር 60 በመቶ የሚሆኑ ሰራተኞቹን የዓመት እረፍት ማስወጣቱን ገልጸዋል።

የተቀሩትም ሰራተኞች አካላዊ ርቀትን እንዲያከብሩና ሲወጡና ሲገቡ የሙቀት ልኬት የሚደረግ ሲሆን ለይቶ ማቆያም ተዘጋጅቷል ይላሉ።

በዚህ ወቅትም አየር መንገዱ የመንገደኞች አገልግሎት በረራውን በመቀነስ የካርጎ ጭነት አገልግሎቱን በማስፋት ላይ ይገኛል።

''ከካርጎው ጎን ለጎን ደግሞ የራሱን አየር ጨምሮ የሌሎች አገሮች አየር መንገዶችን ጥገና በስፋት እያከናወነ ይገኛል'' ብለዋል።

አየር መንገዱ በካርጎ ስራውም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ የህክምና ቁሳቁሶችን በስፋት እያሰራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የአሊባባው መስራችና ባለቤት ጃክ ማ በመጀመሪያ ዙር ለአፍሪካ አገሮች የላኩትን የህክምና ቁሰቀቁስ በስድስት ቀናት ለ51 አገሮች ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

በዚሁ የካርጎ አገልግሎቱም ከአፍሪካ በተጨማሪ በአውሮፓና ቻይና ጭምር ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

እንደ አቶ ተወልደ ገለፃ፤ አየር መንገዱ ቀደም ሲል የካርጎ ጭነት አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩት አውሮፕላኖች በተጨማሪ 8 የመንገደኛ ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ለካርጎ ስራ አሰማርቷል።

አየር መንገዱ እንዲህ አይነት መንገዶችን በመጠቀም ሊያጋጥመው የሚችለውን የገቢ ጉዳት ለመቋቋም እየሰራ መሆኑም አመልክተዋል።

''ችግሩ ከሁለት እስከ ሶስት ወር ብቻ የሚዘልቅ ከሆነ አየር መንገዱ ሊቋቋመው ይችላል'' ብለው ተስፋ አድርገዋል። 
አየር መንገዱን በሚመለከት አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎች እንደሚናፈሱ የጠቆሙት አቶ ተወልደ፤ የዱባይ በረራውን አላቋረጠም መባሉ ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል።

''በርከት ያሉ ከዱባይ የመጡ ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በመንግስት ከተገለጸ በኃላ አንዳንዶች ወደ አየር መንገዱ ጣታቸውን እየቀሰሩ ነው'' ብለዋል።

አቶ ተወልደ እንዳብራሩት፤ 180 ግለሰቦች በዱባይ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆኑ ሌሎች 2 ሺህ 900 ሰዎች ደግሞ የሳዑዲ አየር መንገድ በስምንት አውሮፕላን ቦሌ አየር ማረፊያ ያመጣቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም እንደ ሌሎች አየር መንገዶች በረራ እያደረገ ሲሆን በመጠኑም ወደ አውሮፓና አሜሪካ እየበረረ ይገኛል ተብሏል።
የአየር መንገዱ የጥገና ክፍልም ከመደበኛ ስራው ባሻገር በየሆስፒታሉ ተበላሽተው የቆዩ 30 የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን እየጠገነ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በተስተጓጎለው በረራ የ550 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው በቅርቡ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም