የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያን የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከል አደነቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያን የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከል አደነቀ
ሚያዚያ 7 2012 (ኢዜአ) የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያን የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከል አደነቀ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ በቻይና ዉሃን ግዛት መከሰቱን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ካረጋገጠ በኋላ ኢትዮጵያም የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን ስትሰራ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ የቫይረሱን ቅድመ መከላከል የዓለም አቀፍ ሁኔታን እየተከተለች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራች ትገኛለች ፡፡
ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ብሄራዊ ግብረ ሃይል ከማቋቋመ ባለፈ ለህብረተሰቡ የቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ በመስጠትና በማስተባበር ለበሽታው ምላሽ ለመስጠት እያደረገች ያለውን ርብርብ የዓለም ጤና ድርጅት አድንቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቦሪማ ሳመቡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ለኮሮናቫይረስ ምላሽ ለመስጠት እየሰራች ያለውን የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች አድንቀዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ አገሮች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረው ኢትዮጵያ በቅድመ መከላከል ተግባሯ አድናቆት የሚቸራት መሆኗን ገልጸዋል።
የዓለም የጤና ድርጅትም በአሁኑ ወቅት ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ እደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በአፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት የሚልከውን ቁሳቁስ ለማሰራጨት ኢትዮጵያ ማዕከል እንድትሆን መምረጡንም አስረድተዋል።
''ኢትዮጵያ ወረሽኙ በመጋቢት ወር በአገሯ መግባቱን ካረጋገጠች በኋላ ፈጣን ምላሽ መስጠት ችላለች'' ሰሊ የገለጹት ተወካዩ፤ ''ምላሽ ለመስጠት ያስቻላት በሰራችው ጥሩ የዝግጅት ነው'' ብለዋል።
ድርጅቱም የዝግጅት ስራዎችን በጋራ እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን ከዝግጅት ስራዎች ውስጥ የሙቀት ልየታ፣ በሽታውን መከላከል እና መቆጣጠር፣ የኬዝ አስተዳደር እና ተጋላጭነትን መቀነስ እንዲሁም ህብረተሰብን ማስተባበር ላይ ጥሩ ክንውን በማድረግ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከቀዳሚ አገራት ተርታ ነች።
ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የሚያደርሰውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመደንገግ ጀምሮ የተለያዩ ትላልቅ ውሳኔዎችን ማሳለፏ ይታወቃል።
በተለይም የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የእጅን ንጽህና መጠበቅ፣ የንጽህና ቁሳቁስ ማሰራጨትና በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች አካላዊ ርቀትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ርምጃዎች ተወስደዋል።
ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ የተወሰኑ የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑና የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር የመጫን አቅም 50 በመቶ ብቻ እንዲሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ በመንግስት ከተወሰዱ ርምጃዎች መካከል ይገኙበታል።