ቀጥታ፡

ወሎና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ኮሮናን ለመከላከል የሚውሉ ድጋፎች አደረጉ

ደሴ ኢዜአ ሚያዚያ 7/2012 .የወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫረስን ለመከላከል የሚየግዙ 20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደር የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን ገልጿል ። 
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ቁሳቀሱን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ቫይረሱ የጋራ ትብብርን የሚጠይቅ አደገኛ በሽታ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ግብረ ኃይል አቋቁሞ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከመንግስት ጋር ተባብሮ እየሠራ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲው ከማስተማር ጎን ለጎን ለአካባቢው ህብረተሰብ ባለው አቅም ሁሉ በችግር ወቅት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን 32 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች፣ 720 የህክምና መስጫ ጫማዎች፣ 2 ሺህ 300 ሊትር ሳኒታይዘር፣ አራት ሺህ ብርድ ልብስና አንሶላ እንዲሁም 6 ሺህ 500 ሳሙና የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

ድጋፉ የተሰጠው ለደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ለደቡብ ወሎ ዞን፣ ለኦሮሞና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ነው።

ቫይረሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ጥናቶችን ጭምር በማድረግ  ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ጎን እንደሚቆም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ እብሬ ከበደ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ያደረገው ድጋፍ ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የቁሳቀሱስ አቅርቦት እጥረት የሚያቃልል መሆኑን ጠቅሰው በአፋጣኝ ለየዞኑ እንደሚከፋፈል ገልፀዋል ።

የተሰጠው ድጋፍ በዞኑ በተዘጋጁ ሦስት ለይቶ ማቆያዎች አጋጥሞ የነበረውን ከፍተኛ የግብዓትና የቁሳቁስ ችግር ይፈታል ያሉት ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተወካይ አቶ አሳዬ ገብረስላሴ ናቸው።

በተመሳሳይ መልኩ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ህብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ በማድረግና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸውን ወገኖች በመደገፍ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት በቀን 200 ሊትር የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማምረት ለተለያዩ አካላት ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው ።

ምርቱን በዞኑ ለሚገኙ 560 የጤና ባለሙያዎች፣ ከሦስት መቶ በላይ ለሚሆኑ የሠራዊት አባላትና ለ56 የአምቡላንስ አሽከርካሪዎች ማከፋፈሉን ጠቁመዋል፡፡

በሶዶ ጊቢው የለይቶ ማቆያና የህክምና ማእከላትና አገልግሎት ለሚሰጡ 58  የጤና ባለሙያዎች ጊዜያዊ የመኖሪያ ቤት ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ከቫይረሱ መከሰት ጋር ተያይዞ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ሁለት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው እህል በመግዛት አንድ ሺህ ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ትናንት እንዲከፋፈል አድርጓል ።
የጎዳና ተዳዳሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ተከትሎ በትምህርት ቤቶች መጠለላቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ አንድ ሺህ ፍራሽና የመኝታ ቁሳቁሶች እንዲሁም እህልና የማብሰያና የመመገቢያ ቁሳቁስ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ በጤና ኮሌጁ የህክምና ባለሙያዎች አጠቃላይ የጤና ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን በኮሮና ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደተዘጋጀላቸው ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም