ኦሮሚያ ክልል የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውል ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዝብ ድጋፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ኦሮሚያ ክልል የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚውል ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዝብ ድጋፍ አገኘ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2012(ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል የሚውል እስካሁን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዝብ ከተለያዩ አካላት ቃል ተገብቶ ገቢ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
በአጠቃላይ እስካሁን ቫይረሱን ለመከላከል በክልሉ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መገኘቱን የክልሉ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ገልጿል።
የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ዛሬ ባካሄደው አራተኛ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ባለኃብቶችና ድርጅቶች 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ እስካሁን በክልሉ ከ33 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ስለኮሮናቫይረስ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል።
በዚህም ከ347 ሺህ በላይ የክልሉ ወጣቶች በተለያየ መልኩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።
በጥሬ ገንዘብ ደረጃ በክልሉ ውስጥ የልማት ስራዎችን እያከናወኑ ከሚገኙ ባለሃበቶችና ነዋሪዎች በመጀመሪያ ዙር 46 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኝቷል ነው የተባለው።
በሁለተኛ ዙር 22 ሚሊዮን፣ በሶስተኛ ዙር 11 ሚሊዮንና በአራተኛ ዙር 10 ነጥብ 8 ሚለዮን ብር ድጋፍ መገኘቱን ሪፖርቱ ያመለክታል።
በዛሬው እለት ለክልሉ መንግስት የድጋፍ ካደረጉ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አንድ ሚሊዮን ብር ሰጥቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተባባል ውድነህ ድርጅቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
''በቀጣይ በኮርፖሬሽኑ ስር የሚገኙ ኩባንያዎች በየአካባቢያቸው ላሉ ድጋፍ አሰባሳቢ አካላት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደርጋሉ'' ብለዋል።
ሌላው ድጋፍ ያደረገው የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ድርጅት ሲሆን፤ ድርጅቱም አንድ ሚሊዮን ብርና ሌሎች ድጋፎችን በአይነት አበርክቷል።
የድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ናዚፍ ጀማል ''በዚህ በችግር ወቅት ከሕዝብ ጎን መቆም ግዴታ መሆኑን ሁሉም ሊረዳና ርብርብ ሊያደርግ ይገባል'' ብለዋል።
የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዳባ ደበሌ ድጋፍ ያደረጉትን አካላት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከክልሉ ጎን በመቆማቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
''መንግስትም ላደረጋችሁት ድጋፍ ውለታችሁን የሚከፍል ይሆናል'' ብለዋል አቶ ዳባ።
ክልሉ አሁንም ለበሽታ መከላከል ስራው በተለያየ መልኩ የድጋፍ ማሰበሳብ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።