ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ላይ ያለውን የአያያዝ ክፍተት ማስተካከል ይገባል -የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ ባባባ ሰኔ 25/2010 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ላይ ያለውን የአያያዝ ክፍተት ማስተካከል እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ቋሚ ኮሚቴው አንዳስታወቀው በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ካሉት የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሚታየው የሠራተኞች አያያዝ ክፍተት ከፍተኛ ፍልሰት ለመኖሩና ውጤታማ ላለመሆኑ እንዱ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። በመሆኑም ሠራተኞቹ የደመዋዝ ክፍያ ማነስ፣ የትራንስፖትና የቤት እጦት እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዝ ፍልሰት መኖሩን ደርሼበታለሁ ያለው ቋሚ ኮሚቴው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ኮሚሽኑ ትኩርት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁሟል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሀኑ መኩዬ እንደገለጹት በአገሪቱ  እየተገነቡ ያሉት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አገሪቱ የምትጠብቀውን የውጭ ምንዛሬ ባለማስገኘታቸው ኮሚሽኑ የቅርብ ክትትል በማድረግ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በቅርበት መስራት እንደሚገባም አሳስቧል። ለዚህ የሠራተኞችን ክህሎት በስልጠና በማበልጸግና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ምርት በማሳደግ ባለሀብቱና ሰራተኛው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል። ኮሚሽኑ በ2010 ዓ.ም የአፈጻጸም ርፖርት በአቀረበበት ወቅት የሠራተኞች ፍልሰት መኖሩን  ጠቅሰው በቀጣይ ዓመት ዓለም አቀፍ የስልጠና ተቋም ለማቋቋም እቅድ እንደያዘ ገልጿል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላቸው መኩሪያ እንደገለጹት የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ዋና ዓላማው ለወጣቶች ስራን መፍጠር ላይ ትኩረት መስጠት ቢሆንም ለሚሰማሩበት የስራ ዘርፍም ውጤታማ እንዲሆኑ ክህሎታቸውን ማዳበር ይገባል። ለዚህም ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ብቁ ሠራተኛ በማፍራትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች  58 ሺህ ሠራተኞች ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል። እንደ አቶ በላቸው ገለጻ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንቱ ላይ መጠነኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ሰላም በመስፈኑ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል። በቀጣይም የመድሃኒት እንዲስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚይዝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም