ቀጥታ፡

በትንሳኤ በዓል የፍጆታ እቃዎች እጥረትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ጭማሪና እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ዝግጅትና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ቢሮው የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በበዓሉ የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ዝግጅትና ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ለኢዜአ አንደገለጹት በኮቪድ 19 ሳቢያ የንግድ አንቅስቃሴው እንዳይቀዛቀዝና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የትንሳኤ በዓል መቃረቡን ተከትሎም ገበያው የተረጋጋና የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት የማድረስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በግብርና ምርቶች ላይ እጥረቶች እንዳይከሰት በከተማዋ ካሉ የህብረት ስራ ማህበራት ጋር ውይይቶችን በማድረግና የምርት አቅርቦቱ በስፋት እንዲኖር ለማስቻል ወደ ስራ ተገብቷል።

በፋብሪካ የሚመረቱ የኢንዱስተሪ ውጤቶችን በተመለከተም እንዲሁ ከአምራቾችና፣ አስመጪዎች ጋር ቢሮው በጥምረት እየሰራ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው የአቅረቦት መቆራረጥና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል።

ቢሮው የግብርና ምርቶችን በስፋት ከሚያመርቱ ክልሎች ጋር በመነጋገር ምርት ወደ ከተማዋ በስፋት የሚገባበትና ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የግብርና ምርቶችን በተመለከተ በተመሳሳይ መንገድ ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን አቅርቦቱን ለማጠናከር አየተሰራ መሆኑንም  አቶ አብዱልፈታህ ገልጸዋል።

የፍጆታ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሎ እንደነበር አስታውሰው ይህንንም ለመፍታት ቢሮው የቁጥጥር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ገበያውን የማረጋጋትና ስራ እያከነወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ችግር በሚፈጥሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙም ቢሮው እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በዚህም ረገድ ቢሮው ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት ጋር በመሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግና በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ የታየ ቢሆንም የአብዛኛውን ምርት የዋጋ ጭማሪ መፍታት ተችሏቅል ብለዋል።

ለኮሮናቫይረስ ስርጨት አይነተኛ መንስኤ ነው ተብሎ የተለየው የማህበረሰቡ የግብይት ስርአት ግን አሁንም እምብዛም መሻሻል እንዳላሳየ አቶ አብዱልፈታህ ይናገራሉ።

በከተማዋ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው በተለይ የአትክልት ገባያዎች በሰፋፊ ስፍራዎች እንዲከናወኑ የማድርግ ስራ ተሰርቷል።

የፒያሳውን የአትክልት ተራ ግብይት ወደ ጃል ሜዳ በማዛወር የሰዎችን ጥግግት ለማስቀረት ጥረት ቢደረግም አሁን የሚቀሩና መሰራት ያለባቸው ተግባራት መኖራቸውን ተናግረዋል።

በትንሳኤ በዓል የቁም እንስሳትና ሌሎች ግብይቶች በስፋት ስለሚከናወኑና ለኮሮናቫይረስ መስፋፋትም ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግም ሃላፊው መክረዋል።

ጉዳዩን ችላ በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚተላለፉ አካላት ሲያጋጥሙም እርምጃ ከሚወስዱ አካላት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም