ኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ
አዲስ አበባ 25/ 2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከፍተኛ ኃይል የተቀላቀለበትና ሽኩቻ የበዛበት ነበር። በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥርና ወደ ግብ በመቅረብ ከተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ተሽሎ ታይቷል። ከጨዋታው በፊት ጥሎ የነበረው ከባድ ዝናብ ሜዳውን በማጨቅየቱ ተጋጣሚዎቹ ኳስ ይዘው ለመጫወት እንዲቸገሩ አድርጓል። ኢትዮጵያ ቡና ወደ ተጋጣሚው ግብ በመቅረብ የተሻለ ሆኖ ያመሸ ሲሆን በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ ረጅም ኳስ በመጠቀም ወደ ተቃራኒ ቡድን ለመቅረብ ሙከራ አድርጓል። በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በመውደቅ ሰዓት ሲያባክኑ ታይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቶ በመውጣቱ ወደ መሪዎቹ የመቅረብ ዕድሉን ያመነመነ ሲሆን የወራጅነት ስጋት ያለበት ድሬዳዋ ከተማ ወሳኝ የሆነ አንድ ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል።