ቀጥታ፡

የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የ200 ሚሊዮን ዶላር የህክምና ቁሳቁሶችን ግዥ ሊፈጽም ነው

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 6/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለኮቪድ-19 መከላከያ ግምታዊ ዋጋቸው 200 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶችን ግዥ ሊፈጽም ነው።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ተስፋአለም አድራሮ ለኢዜአ እንዳሉት ኤጀንሲው የኮሮናወረርሽኝን ለመከላከል የህክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ተቋማት እያሰራጨ ነው።

ኤጀንሲው የገዛቸውን ቁሳቁሶች ከማሰራጨት በተጨማሪ በአስቸኳ ግዥ እየፈጸመ እንደሚገኝ አብራትዋል።

የጤና ባለሙያዎች እራሳቸውን ከበሽታው የሚከላከሉበት 13 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በቅርቡ ወደ መጋዘን ገብተው እንደሚሰራጩም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 200 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ግዥ ለመፈጸም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የህክምና ቁሳቁሶች አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ የሚደረግባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ቁሳቁሶችን በፍጥነት ግዥ ፈጽሞ ለጤና ተቋማት ለማሰራጨት የግዥ ጊዜን ማሳጠርና የተለዩ አቅራቢዎች እንዲሳተፉ እየተደረገም ነው።

ቀደም ሲል 35 ቀን ይፈጅ የነበረውን ዓለም አቀፍ ግዥ በ15 ቀን እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።

ኤጀንሲው የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች፣ 21 ሚሊዮን የእጅ ጓንት አሰራጭቷል።

በተጨማሪም ከአሊባባና የቻይና መንግስት እንዲሁም ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የተኙ 590 የሙቀት መለኪያ ለሁሉም ክልሎች አሰራጭቷል።

ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች የተገዛ 700 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር ያሰራጨ ሲሆን 200 ሊትር የንፅህና መጠበቂያ አልኮልም እያስገባ ይገኛል።

በተጨማሪም ከ350 በላይ የኦክስጅን ሲሊንደር ለክልሎች እየተሰራጩ መሆኑን አንስተዋል።

የግል ባለሃብቱ የኮሮናቫይረስን ለመላከል እያደረገ ያለውን ድጋፍ በህክምናው ዘርፍም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም