ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ለትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳት ያለፍቃድ ማንቀሳቀስና ማገበያየት እንደማይቻል ተገለጸ

መቀሌ፤ሚያዝያ 06/2012 (ኢዜአ)በትግራይ ክልል የትንሳኤን በዓልን ምክንያት በማድረግ የእርድ እንስሳትን ያለፍቃድ  ማንቀሳቀስና ማገበያየት እንደማይቻል የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ገለጸ። 

በኮማንድ ፖስቱ የኢኮኖሚ ግብረ ኃይል  አስተባባሪ ዶክተር መብራህቱ መለስ በሰጡት መግለጫ በበዓሉ ምክንያት የሚካሄድ የእንስሳት ግብይት ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት በማያጋልጥ መልኩ እንዲከናወን መመሪያ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የእርድ እንስሳት ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሰው ከኮማንድ ፖስት ፈቃድ በሚሰጣቸው አካላት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።

ፈቃድ የሚሰጣቸው አካላትም ወደ ገበያ የሚያቀርቧቸው የእርድ እንስሳት ብዛት መወሰኑን አመላክተው፤ የሰዎችን ጥግግትና ቅርርብ ለመቀነስ ለእርድ የሚሆኑ ሰንጋዎችን አንድ አቅራቢ ከ20 በላይ  ለገበያ  እንዲያቀርብ መወሰኑን ገልጸዋል።

አንድ አቅራቢ 100 እና ከዚህ በላይ በጎችና ፍየሎችን ለገበያ እንዲያቀርብ መመሪያው የሚያስገድድ መሆኑን የገለጹት የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ "ዶሮዎች ደግሞ ከ50 በላይ  እንዲሆኑ ተወስኗል" ብለዋል።

ዓላማውም የአቅራቢው ሰው ቁጥር ቀንሶ  የእርድ እንስሳትን በማብዛት በሽታውን ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል።

ፍቃድ የሚሰጠውም አቅራቢው ለገበያ ያመጣቸውን የእርድ እንስሳት ብዛት በመቁጠር በመመሪያ መሰረት መሆኑ ሲረጋጋጥ  እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህ ውጭ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ግለሰብ ንብረቱ እንደሚወረስ አስታውቀዋል።

በሁሉም የእንስሳት ገበያ ማዕከላት የውሃ ፣ሳሙናና ሌሎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የኮማንድ ፖስቱ አባል ዶክተር አብርሃ ብስራት ናቸው።

በክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የከተሞች አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር አቶ አዳነ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው ለበዓሉ በአንድ የገበያ ማዕከል መሰባሰብ ቀርቶ በየአከባቢው  ግብይት እንዲካሄድ መወሰኑን ተናግረዋል።

ግብይቱም ከሚያዝያ 6/2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ዋዜማ ሚያዚያ 10/2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት ከሰዓት በፊት ብቻ እንደሚሆን ተመልክቷል።

በከተሞች የእርድ እንስሳት እጥረት እንዳያጋጥም ፈቃድ ያላቸው ህብረት ስራ ማህበራትና  ነጋዴዎች በአቅርቦቱ እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም