‘’የዘመኑን ጠላት’’ ለመርታት - ኢዜአ አማርኛ
‘’የዘመኑን ጠላት’’ ለመርታት
ከብርሃኑ ተሰማ (ኢዜአ)
አዲሱ ዓመትና ኮቪድ 19
ዓለም የአውሮፓውያኑ 2020 ሲገባ ከሚጠብቃቸው ዓበይ ተግባራት አንዱ በስፖርቱ ዓለም የ‘’ቶኪዮ 2020’’ን ነበር። የጃፓኗ ርዕሰ ከተማ ኦሊምፒክ የምታስተናግድበት ዝግጅት። ዝግጅቱ አገሮች በየአራት ዓመታት ልዩነት የሚገናኙበት ታላቅ መድረክ ነው። በኦሊምፒክ ውድድሮች በሜዳሊያዎች ዓይነትና ቁጥር መበላለጥ የአገሮችን የስፖርት ደረጃ ያመላክታል። ሆኖም የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎች ያላገኙ ተወዳዳሪዎች ወደ አገሮቻቸው የሚመለሱት በተሳትፏቸው ኮርተው ነው። ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት።
ታዲያ ዘንድሮ ለዝግጅት መልፋት የማያስፈልገው፣ ሜዳሊያዎችን ዓይነትና ብዛት ማግኘት የማያስጨንቀው፣ አሸናፊነትም ሆነ ተሳታፊነት ሳይገድበው የውድድር መድረኮችን ያሰረዘ ክስተት ብቅ ብሏል። የዓለምን ሕዝብ ቤት የሚያንኳኳ እንግዳ መስሎ ጠላት ከገባም ውሎ አድሯል።
በዚሁ ድንገተኛ ወራሪ ሳቢያ ኦሊምፒክን ጨምሮ በየሁለት ዓመቱና በየዓመቱ የሚካሄዱ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ወደ ሚቀጥለው ዓመት ለመሸጋገር ተገደዋል። ዓለም ጤና ስትሆንና ስትረጋጋ ሁሉም ነገር ይደረስበታል በማለት መሆኑ ነው። አገሮችን ወክለው በመወዳደር ሜዳሊያዎችን እንሰብስበለን ብለው የነበሩ እጅ እግራቸውን ሰብስበው፤ ለውድድር ራሳቸውን ለዓመታት ያዘጋጁ ስፖርተኞችም ጭምር የዛሬው ፈተና አልፎ መልካም ጊዜ ይመጣል በሚል ተስፋ በቤታቸው ተቀምጠዋል።
አዎን ዓለማችን ኦሊምፒክና የስፖርት እንቅስቃሴ ለማካሄድን አትችልም። መላው የሰው ዘር ሕይወት አደጋ ውስጥ ወድቋልና። ሰው ጨራሽ ስውር ኃይል ሆኖ መጥቷል።
ኮቪድ 19 ወይም ኮሮናቫይረስ ፍጡራንን ለማጥፋት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በማስከተል ጭምር ጦርነት ከፍቷል። የጦርነቱ ግብ ከመግደል በተጨማሪ፣ ባልን ከሚስት፣ ልጆችን ከወላጆች፣ ጓደኛሞችንና ዘመዳሞችን መነጣጠል፣ እነደ አጠቃላይም ማህበራዊ መስተጋብርን በማስቀረት የዓለማችን ፈተና ሆኖ ብቅ ካለ ከ100 በላይ ቀናትን አስቆጥሯል።
ሰላምታውን ሞቅ አድርጎ የሚያቀርበው የአገሬ ሕዝብ ወዳጅና ዘመድን አገላብጦ መሳም ይቅር ሲባል፤ ትከሻ ለትከሻ መነካካትም መከልከሉ ሲነገረው፣ ይህም ቢቀር በእጅ መጨባበጥ ‘’አይቻልም’’ ሲባል ግራ ገብቶታል። አንዳንዶች ያለመተማመን ሌሎች ደግሞ መጠላት ተደርጎ ወስደውታል። ሆኖም መድኃኒት የለሹ የዘመኑ ወረርሽኝ ያመጣው ከባድ የሰው ልጆች ፈተና መሆኑ ሲገባቸው አማራጭ የለም ብለው ተቀብለውታል።
አሁን ዓለም እየገጠሟት ያሉት ችግሮች ሳይወገዱ የገጠማት የህልውና ፈተና በየዕለቱ በሚወጣ መረጃ ይገለጻል። አንዳንድ ወገኖች መረጃውን ሰብዓዊነትን የሚነካ ከዚያም አልፎ አንድን አገር ወይም ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥላቻ በመሰንዘር ሲያስተላልፉት ይስተዋላል ‘’የሞት እሽቅድድም/ ሻምፒዮና‘’ የለም። የቁጥሮቹ መበላለጥ የሰው ልጆችን ጉዳት አመላካች ነው። ቁጥሩ ሲያድግ ማዘን ነው ያለብን፤ ምክንያቱም ’’ነግ በእኔ’’ በመሆኑ።
በሽታው ያስከተለው ሞትና ስርጭቱን ተከትሎ የሚወጣው አኅዝ የችግሩን ስፋት፣ ክብደትና ጥልቀት ያሳያል። አዝማሚያዎችን ለመገመት መነሻ ይሆናል። በተረፈ እዚያም ያለው እሳት እዚህም ሊነድ እንደሚችል አውቆ ቢቻል በሽታው ወዲህ እንዳይደርስ፤ ከመጣም ፈጥኖ ጉዳቱን ለመቀነስ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
ያልተጠበቀው ‘’አስናቀ’’
ዓለምን እያናጋ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን አንድ አድርጓታል። ሀብታምን ከድሃ አልለየም። ትልቅም ትንሽም አላለም። ትናንት ሩቅ መስሎ በታየበት አገር ዛሬ ለመግባት ፓስፖርትና ቪዛ አላስፈለገውም። የዓለም መሪዎች ‘’ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አጋጥሞ የማያውቅ’’፣’’ከቫይረሱ ጋር ጦርነት ገጥመናል’’ የተባለለት የዘመኑ በሽታ ምድራችንን የገጠማት በሽታ የናቁትን አስንቋል። መናናቅን በዕውቀት ለመተካት ትጋት ይጠይቃል።
ኮቪድ 19 ’’ያላወቁ አለቁ’’ ብቻ ሳይሆን፤ እያወቁ ማለቅም እንዳለም አስተምሯል። መናቅና ቸልተኝነት ዋጋ እንደሚያስከፍሉም ተምረንበታል። ’’የዘመኑን ጠላት’’ ለመርታት ጥሩ መንገዶች አይደሉም። ቫይረሱ በቻይናዋ ሁቤይ ክልል ተነስቶ ካዳረሳት በኋላ፣ በአውሮፓና አሜሪካ እልቂት ለማስከተል የፈጀበት ጊዜ አጭር ነበር። እስያና አፍሪካን ጨምሮ በሌሎቹ አህጉሮች ለመንሰራፋት ደግሞ የጠየቀው ጥቂት ሳምንታትን ብቻ ነው።
ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰው ልጅ ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል። ሞትን ባልታሰበ ጊዜ ወደ ቤት ገብቶ መቶ ሺዎች ሞቱበት። አሁንም ሰዎች እንደ ቅጠል መርገፋቸውን ቀጥለዋል። የጤና ተቋማት ጥራትና ብቃት ከፍተኛ መሆን፣ የጤና ባለሙያዎች የዕውቀት ደረጃና ችሎታ መላቅም አልገታውም።
ቫይረሱ በፍጥነት ስለሚራባም የጤና ተቋማት ከነበራቸው ዝግጅት ጋር ባለመመጠኑ ታማሚዎች በሐኪሞች ዓይን ሥር ዓለምን ተሰናብተዋታል። በአሳዛኝ ሁኔታ ዳግም ላይመለሱባት ተለይተውናል።
ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው መስዋዕት የሆኑ፣ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በበሽታው የተያዙ የጤና ባለሙያዎች በርካታ ናቸው። በጣልያን 60 ሐኪሞች በሞት ተለይታዋል። በስፔን ከ12 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በበሽታው መያዛቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ገልጸውልናል።
የችግሩ ዋነኛ ምክንያቶችም የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ጉድለትና እጥረት እንዲሁም በሐኪሞች ላይ የሥራ ጫና መብዛት እንደሆነ ተመልክቷል። ከዚህም የተነሳ ሐኪሞች ድጋፋቸውን ፍለጋ የመጡ ታማሚዎች ሲሞቱ ’’አይ ወገኔ!’’ ብለው ከንፈር ከመምጠጥ በላይ ምንም ማድረግ ያልቻሉበት ሁኔታ በሰው ልጆች የገጠመ ሌላው ‘’ክፉ ቀን’’ ተብሎ በታሪክ እየተመዘገበ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅትና ማሳሰቢያዎቹ
የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ 19ን እንድንጠቀቀው ተደጋጋሚ መልዕከቶች ያስተላለፈ ድርጅት ነው። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሽታውን ለመከላከል በግላቸው ባደረጉት ጥረት ጭምር ሙገሳና አድናቆት ተችሯቸዋል። ሆኖም ከድርጀቱ የሚሰጡት ማሳሰቢያዎች በተለይ በሰለጠነው ዓለም ተገቢውን ትኩረት ያገኙ አይመስልም። በኢኮኖሚው ያደጉት አገሮች ዜጎች ሕይወት የሚነጥቅ ጠላት መምጣቱን የተረዱትም አይመስልም። የድርጅቶቹን መልዕክቶቹን ባለመተግበራቸው እንደሆነ በቫይረሱ የተጠቁትንና ሕይወታቸው የተነጠቁትን አኅዝ ማየት ብቻ በቂ ነው።
ቢያንስ ከቻይና ተምሮ በሽታውን የሚያደርሰውን ጉዳት አልቀነሱም። ዛሬም ሕይወት እንደ ዋዛ ያለ ጊዜዋ እየተጓዘች ነው። አሁንም በበሽታው የሚያዙ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ለሕይወት ዋጋ ያልሰጠ ዳተኝነትና ቸልተኝነት ባደጉት አገሮች መንግሥታት ተስተውሏል። ዜጎች ‘’አውጣን’’ ብለው ፈጣሪያቸውን ከመማጸን በላይ፤ ምንም ማድረግ አልቻሉም።
ዛሬ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ ሆቴሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትላልቅ ሕንጻዎች፣ የእምነት ተቋማት የጦር መርከቦች ሳይቀሩ ወደ ሆስፒታልነት እየተቀሩ ነው። ይሰናበቱባቸዋል። ሐኪሞች ሕይወት ለማትረፍ ይሯሯጡባቸዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይታከሙባቸዋል። ያገገሙባቸዋል። ካልተቻለም ይህቺን ዓለም ይሰናበቱባቸዋል። ሞት ለጊዜው አሸንፏል። እስከወዲያኛው እንደማይዘልቅ ግን እምነትና ተስፋ አለ።
‘’ከምቀርብሽ ብዬ…….’’
የኮሮናቫይረስ ብዙም ሳይረፍድበት አፍሪካን ‘’መጣሁልሽ’’ አላት። ብዙም የጤና መሰረተ ልማቶች ተሟልተው በማይገኙባት፣ ብዙ ሰዎች በድህነት ላይ በሚኖሩባት አህጉር የወረርሽኙ መከሰት ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ ርግጥ ነው። የኮሮናቫይረስ ድንበር የለሽ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ብሄርና ቀለም የሚለይ አልሆነም። የሀብት መጠን መለያየትም ሊመክተው አልቻለም።
የአፍሪካ አገሮች ’’የማይቀረው’’ እንግዳቸውን ለማስተናገድ ምን ያህል እንደተዘጋጁ የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው። አህጉራዊው የጤና ድርጅት ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ግን እርግጥ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ አስተባባሪነት ከዓሊ ባባ ድርጅት ባለቤት ጃክ ማ በሽታውን ለመከላከል የሚረዳ ድጋፍ ለ54 የአፈሪካ አገሮች እየተከፋፈለ መሆኑም ተገልጿል። ድርጅቱ ለሁለተኛ ጊዜም ድጋፉን ሰሞኑን አድርጓል።
የአፍሪካ ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ፣ ማህበራዊ ሁኔታና የዕድገት ደረጃ አኳያ በወረርሽኙ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል የሚል ግምት እየተሰነዘረ ነው። በዚህ ላይ የጤና ድርጅቶች ያላቸው የሰው ኃይል፣ የሕክምና መሣሪያዎች በዓይነትና በጥራት ደረጃ አለመገኘት ይህንን ዓለም አቀፍ በሽታ ለመከላከል የአፍሪካን አቅም በእጅጉ እንደሚፈታተን ለመገመት ቀላል ነው።
በሽታው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲሁም ፖሊቲካዊ ቀውስ ያስከትላል። ይህም አፍሪካ ካለችበት ኋላ ቀርና አዝጋሚ የዕድገት ደረጃ እንድታሽቆለቁል ያደርጋታል የሚል ስጋት አሳድሯል። ስለዚህም ኮቪድ 19 በአህጉሪቱ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል መንግሥታት ሕዝቡን፣ የሲቪክ ማህበራትንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያስ?
የኢትዮጵያ መንግሥት በሽታውን ለመከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስም በተዘረጋው አደረጀጀት በተመሳሳይ መልኩ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። መንግሥት የጤና ማዕከላትን ደረጃና አቅም በማሳደግ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን በለይቶ ማቆያዎች፣ በበሽታው ለተያዙ ደግሞ ለይቶ ማከሚያዎችን አዘጋጅቷል።
የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙ በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሙያዊና የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ይልቁንስ ኮቪድ 19 በከባድ ደረጃ ጉዳት በደረሰባቸው አገሮች በሙያ አጋሮቻቸው ያደረሰው ዓይነት ጉዳት እንዳያስከትል ‘’ራሳችሁን ጠብቁ እኛንም ከአደጋ ጠብቁ’’ እያሉ እየተማጸኑም ነው። የእኛ መኖር፣ የእናንተም መኖር ነውና እንረዳዳ የሚለው የሃኪሞቻቸን ውትወታ ሰሚ ማግኘት ያለበት ትክክለኛ መልእክት መሆኑ እርግጥ ነው።
ሚኒስትሮች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አርቲስቶች በየአደባባዮች በመዘዋወር የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሕዝቡ የበሽታውን ምንነትና የመከላከያ መንገዶች እንዲያውቅ እገዛ እንዳደረገለት ይታመናል። በአገር ደረጃ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የገንዘብ፣ የእህልና ማረፊያ ቦታዎችን በመለገስ ድጋፍ እየተደረገም ነው። ክልሎችም የሕዝቡን ድጋፍ በማስተባበርና በማቀናጀት ሚናቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። አበረታች ጅምር ሕዝብና አገርን ከአደጋ ለማዳን በመታየት ላይ ነው ማለት ይቻላል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ጠያቂነት ለመላው አፍሪካ የተረፈ ከዓሊ ባባ ፋውንዴንሽን የተገኙ የሕክምና መሣሪያዎችም ድጋፍ ሰጪውንም ብቻ ጠያቂውንም ጭምር እንደሚያስመሰግን መግለጽ ተገቢ ይሆናል። የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለታዳሚዎች ወቅታዊ መረጃ በመስጠትና በማወያየት ሚናቸውን እየተወጡ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ተቋማቱ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ዝግጅቶቻቸውን በተለያዩ መንገዶች አዳብረውና አበልጽገው ሳቢና ማራኪ የማስተማሪያ መንገዶች ቢፈጥሩ ውጤታማ የመከላከል ሥራው ውጤማታማ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ምን እናድርግ?
ከቫይረሱ መከላከያ መንገዶች አንዱና ዋነኛው እጅን መታጠብ ነው። እጅ መታጠብ ከግል ንጽህና መጠበቂያ መንገዶች አንደኛው ሆኖ ለዘመናት የኖረ ሳይንስ ነው። የአሁኑ ቫይረሱ በሚያስከትለው ጥቃት አንጻር ድግግሞሽ መጠየቁ ለየት ያደርገዋል። እጅ መታጠብ ማንንም አይጎዳምና ባህላችን አናድርግ። ችግሩ እርግጥ ነው እዚያም እዚህም የውሃ እጥረት መኖሩ ባይካድም ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይጠበቅብናል።
አካላዊ መራራቅን በመጠበቅ መንቀሳቀስ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረቱ መቀጠል አለበት። ጠዋትና ማታ በተገናኘ ቁጥር በመጨባበጥና ከንክኪ ያልወጣ ሰላምታ ያለውን ሕዝብ ‘’አትነካካ’’ ማለት ከባድና አስቸጋሪ ነው። ቶሎ ለመልመድም ያዳግታል። ቢሆንም በሕይወት ለመቀጠል ምርጫው አትንካ የተባለው አለመንካት መሆኑን ማስተማር ያስፈልጋል።
በሸታውን ተጨንቀን ልናመልጠው አንችልም። ጭንቀትም መረበሽንና አለመረጋጋትን እንዳያመጣ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ጭንቀት ለየትኛውም ሕመም መድኀኒት ሲሆንም አልታየም። ኅብረተሰቡ ያደራጃቸው ዕድሮች፤ ዕቁቦች፤ ማህበራትና ሌሎችም አደረጃጃቶች በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ መደገፍ ይጠበቅባቸዋል።
ትዝብት
የአገራችን በርካታ ታዋቂ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ተምሳሌትነታቸው እምብዛም ሆኗል። ሕዝቡን ያለመታከት ሲያስተምሩ አልታዩም። ለበሽታው መከላከያ ድጋፍ ሲያደርጉም በብዛት አልታዩም የሚሉ ታዛቢዎች አሉ። ሕዝብን ለመምራትና ለማስተዳደር በእንደዚህ ዓይነት የችግር ወቅት ከኅብረተሰቡ ጎን መቆም ተገቢ ነው። በችግሩ ወቅት ‘’አለሁልህ’’ ያላሉት ሕዝብ በምርጫ ጊዜ ‘’አላውቃችሁም’’ ሊልም ይችላል። ማንን ይዞ ጉዞ!!!
ስናጠቃልለው
አሁን ላይ ዓለም ፈተና ውስጥ ወድቃለች። በተስፋ የጠበቀችው አዲሱ ዓመት የፈረንጆቹ 2020 ሌላ የዓለም ጦርነት የገባችበት ዘመን ዓይነት ሆኗል። በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች አስደንጋጭ ሆነዋል። ሞትና ሕይወት የተፋጠጡበት ጊዜ ገጥሞናል። ’’ቶኪዮ 2020’’ ነገሮች ሲስተካከሉ እንዲካሄድ ወደ ቀጣዩ ዓመት ተሸጋግሯል። ለዚህ ውድድር በአካልም ይሁን በቴሌቪዥን ለመታደም ያልታደሉ በርካቶች ዛሬ ላይ በቫይረሱ ምክንያት ረግፈው ቀርተዋል።
አሁንም ራሳችንንም ይሁን ሌሎችን ማትርፍ የምንችልባቸው የመከላከያ አማራጮች አሉና ጊዜ ሳናባክን ወደ ተግባር መግባት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። እጅን መታጠብ፣ አለመነካካትና በቤት መቀመጥ ዋነኞቹ የቫይረሱ መከላከያ መንገዶች ናቸው። በሽታውን በመቆጣጠር መልካም ተሞክሮ ያላቸውን አገሮች ልምድ መውሰድም ጠቃሚ ነው።
መንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች የሚሰጡንን አቅጣጫ አክብረን በመፈፀም መጀመሪያ ራሳችንን ከሞት እናተርፋለን። አገራችንን ከእልቂት እናድናለን። አልፎም ለአፍሪካ ሞዴል ልንሆን እንችላለን። ኢትዮጵያዊያን በወራሪ ጠላት መሸነፍ አናውቅምና አሁንም ለወራሪው ቫይረስ እጅ እንዳንሰጥ ቃል እንግባ። ሰላም ለሁላችን!