በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ ከ 11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ ከ 11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኘ
ጋምቤላ ፣ሚያዚያ 6/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከ11ሚሊዮን 600 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መገኘቱ ተገለጸ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ና የሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ተንኳይ ጆክ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድጋፉ የተገኘው በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ነው።
በተጨማሪም ከባለሃብቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጀቶች የተለያዩ ቁሳቁሳች በድጋፍ መገኘቱንም አመልክተዋል።
ከቁሳቁሶቹም መካከል የሙቀት መለኪያ መሳሪያ፣ የእጅ ጓንት፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ይገኙበታል።
ግብረ ኃይሉ የተጠናከረ ንቅናቄ በመፍጠር ከባለሀብቱ፣ ከንግዱ ማህበረሰብና ከሌሎችም አካላት ተጨማሪ ገቢ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አቶ ተንኳይ አስታውቀዋል።
የሃብት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ዘግይቶ ቢጀመረም እስካሁን የተገኘው ገቢ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው መላው የክልሉ ህዝብ ቫይረሱን ለመከላከል ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።