ቀጥታ፡

የሎጂስቲክ ሥርዓትን ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ውጤት አለመገኘቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 በኢትዮጵያ የሎጂስቲክ ሥርዓት በመለወጥና አሰራርን በማሻሻል ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተፈለገው ውጤት ማምጣት ያለመቻሉ ተገለጸ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የ2010 በጀት ዓመት የ11 ወራት አፈፃፀምን ሪፖርት ገምግሟል። የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት የሎጂስቲክ ሥርዓት ለመለወጥና አሰራሩን ለማሻሻል የተደረገው ጥረት የተፈለገው ውጤት አላመጣም። ኢትዮጵያም በሎጂስቲክ አፈፃፀም ኢንዴክስ የነበረችበትን 126ኛ ደረጃ ለማሻሻል አልቻለችም። ለዚህም የቀልጣፋ ሎጂስቲክ ስርዓት አለመዳበር፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆንና ህጎችን በሚገባ ተግባራዊ አለማድረግ በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የማሪታይም ዘርፍ የባህር ሰራተኞችን ቁጥር ወደ 15 ሺ ቢታቀድም ክንውኑ 7 ሺህ 190 መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የእቅዱን 48 በመቶ ብቻ መፈጸሙን እንደሚያመለክት ተናግረዋል። ሪፖርቱን ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው በወደብ ላይ ተከማችተው የሚገኙ ዕቃዎች በወቅቱ ባለመነሳታቸው አገሪቷ ለከፍተኛ ወጪ የተዳረገችበትን  ምክንያት እንዲብራራ ጠይቋል። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ፤ በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ ወደብ ከአንድ ነጥብ አራት ቶን በላይ ዕቃዎች መከማቸቱን አውስተዋል። ይሄም ከዚህ ቀደም ከተለመደው ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተው፤ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች በወቅቱ ለተጠቃሚ ባለመድረሳቸው "እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል" ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት ለአፈር ማዳበሪያ ቅድሚያ በመስጠት በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ተናግረው፤ የቀረው የዕቃ ክምችት በሚቀጥለው ወር መጨረሻ በርብርብ እንዲገባ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የወደብ ክምችቱና የቅንጅታዊ አሰራር መዳከሙ የሎጂስቲክ ስርዓቱ ችግር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ይሄም በአሁኑ ወቅት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የአገሪቷ የትራንስፖርት ፖሊሲ የሎጂስቲክ ስራቴጂ "ችግርን ይፈታል" የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት አገር አቀፍ የትራንስፖርት ረቂቅ ፖሊሲ፣ የሎጂስቲክ ስትራቴጂ፣ የመንገድ ትራንስፖርት የፍጥነትና የክብደት ወሰን ረቂቅ አዋጆች፣ የተሻሻለ የተሽከርካሪዎች መመሪያ ደንብ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ተጠቁሟል። የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሚል አህመድ ፖሊሲውን ጨምሮ ለቅንጅታዊ አሰራርና የተሻለ ስራ ሊያሰሩ የሚችሉ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በወቅቱ ጸድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡም አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም